ባለስልጣን መስሪያቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ፈንድ አሸናፊ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡

በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 አንቀጽ 86 መሰረት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሚተዳደር የሲቪል ማህበረሰብ ፈንድ እንደሚቋቋም ተደንግጓል፡፡ ባለስልጣን መስሪያቤቱም ይህንኑ በሚመለከት ባወጣው ‹‹የሲቪል ማህበረሰብ ፈንድ አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 848/2014 መሰረት ለሃገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፈንዱ ድጋፍ ለማድረግ በቀን 10/06/2014 ዓ.ም ግልጽ ፕሮፖዛል መቀበያ ጥሪ ማስታወቂያ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያወጣ ሲሆን በጥሪው ማስታወቂያ መሰረት 95 /ዘጠና አምስት/ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለውድድር ቀርበው በመመዝገብ በቅድመ ምዘና እና ቴክኒክ ኮሚቴው ውሳኔ መሰረት ሶስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመረጣቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት ዛሬ በውድድሩ አሸናፊ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር የድርጅቶቹን እና የተቋሙን ተግባርና ሃላፊነት የያዘ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ ፈንዱ በሁለት ዙር የሚለቀቅ ሲሆን የመጀመሪያዎቹን ሶስት ወራት በመመልከት የሚቀጥለው 50 ፐርሰንት የሚለቀቅ መሆኑ በስምምነት ስነ ስርዓቱ ላዩ ተገልጿል፡፡ በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ ድርጅቶች በሰጡት አስተያየት ሌሎች ሃገራት ላይ ያለ ልምድ መወሰዱ ፣የውድድር ሂደቱ ግልጽ መሆኑ አበረታች ነው በማለት ተቋሙ የሰጠንን ሃላፊነት ሙሉ በሙሉ ለመወጣት እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡


ለ2ተኛ ጊዜ የተዘጋጀው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንትን (CSOs Week) ዛሬ ተጠናቋል፡፡

ባዛርና ኤግዚቪሽኑ ከጉብኝት እና ከመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ጎን ለጎን በአራት ርዕሰ ጉዳዬች ላይ የፓናል ውይይት ተደርጓል ፡፡ ውይይቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰላም ግንባታ ላይ ያላቸው ሚና፣ከአዲሱ አዋጅ በኋላ የመጡ ለውጦች እንዲሁም ስርዓተ ጾታ እና ተያያዥ ጉዳዬች ተዳሰዋል፡፡ በመዝግያ መርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለምአንተ አግደው የተገኙ ሲሆን በንግግራቸውም ይህ ባዛርና ኤግዚቪሽን በመዘጋጀቱ ለዘርፉ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን እና ባዩት ስራ መደሰታቸውን ገልጸው ሚኒስትር መስሪያቤታቸው ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚፈልጉት ድጋፍ ሁሉ ከጎናቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው የተሳካ ባዛርና ኤግዚቪሽን በመዘጋጀት ሂደት አስተዋጽኦ ላደረጉ ድርጅቶች ፣ተሳታፊዎችና አዘጋጅ ኮሚቴዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡


ሁለተኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባዛርና ኤግዚቪሽን በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡

ንቁ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም፣ለዲሞክራሲና ለልማት በሚል መሪ ቃል ለ2ተኛ ግዜ ዛሬ በሒልተን ሆቴል ተጀምሯል፡፡ ኤግዚቪሽኑን ዶ/ር ጌዲዬን ጢሞቲዬስ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ኮሚሽነሮች፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዬች፣የተለያዩ የግል ሴክተሮች እና በርካታ እንግዶች በተገኙበት ተከፍቷል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ከዛሬ ጀምሮ አስከ ቅዳሜ ሰኔ 25/2014 ዓ.ም ድረስ ይቆያል አርሶም መጥተው እንዲጎበኙ ጋብዘነዎታል፡፡


ለ2ተኛ ግዜ የተዘጋጀው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንትን (CSOs Week) በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

ፕሮግራሙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ካውንስል ጋር በጋራ በመሆን የተዘጋጀ ሲሆን ዝርዝር ሂደቱን በተመለከተ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እና የካውንስሉ ሃላፊ አቶ ሄኖክ መለሰ ማብራሪያ ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በመግለጫው በሰጡት ማብራሪያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ ጋር የጀመሩትን መልካም ግንኙነት አጠናክረው እንዲቀጥሉና መብትና ግዴታውን በውል የተረዳ፤በውይይት በምክንያታዊነት የሚያምን የነቃና በነጻነት የተደራጀ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተጀመሩ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስራዎች ሊጠነክሩ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በተመሳሳይ የካውንስሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ ባስተላለፉት መልዕክት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ፕሮግራም ከመንግስት፣ከግሉ ዘርፍ እና ከብዙሃን መገናኛ ጋር ያላቸውን እና የሚኖራቸውን ግንኙነት ከምንግዜውም በበለጠ ከማጎልበቱም በላይ በጋራ ጉዳዬቻቸው ላይ በአንድነት ለመስራት ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ምክር ቤቱ በጽኑ ያምናል ብለዋል፡፡ ሃላፊዎቹ ሌሎች ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ባዛርና ኤግዚቪሽኑ ከሰኔ 23 አስከ 25 /2014 በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል የሚካሄድ ይሆናል፡፡


‹‹ማህበራዊ ተጠያቂነት የመንግስት አገልግሎት ከሙስና የፀዳና ውጤታማ እንዲሆን በማስቻል በአንድ አገር ውስጥ ሁለንተናዊ ልማት እንዲረጋገጥ የሚያደርግ ነው ሲሉ አቶ ፋሲካው ሞላ ተናገሩ››

በሁሉም ክልሎች በሶሻል አካውንተብሊቲ ዙሪያ ስልጠና ለመስጠት የተያዘው እቅድ በደቡብ ፣በሲዳማ ፣ሐረር እና አፋር ክልሎች እየተተገበረ ይገኛል፡፡
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አርባ ምንጭ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመነሳት እንዲሁም ካላቸው ዘርፈ ብዙ ሃላፊነት በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ላይ የማህበራዊ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ የመሪነት ሚና መጫዎት የሚችሉ በመሆኑ በሁሉም ክልሎች ስልጠናው መዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡ ማህበራዊ ተጠያቂነት ሲባል ዜጎች በማንኛውም ደረጃ በሚገኝ የመንግስት አገልግሎት ገንቢ ተሳታፎ የሚያደርጉበት ሂደት ሲሆን በተሳትፎውም የመንግስት አገልግሎት ግልፅ፣ ተጠያቂነት ያለበት፣ ውጤታማ የሆነ፣መልካም አስተዳደርን በማስፈን የመንግስት አስተዳደር እንዲሻሻል እንደሚያደርግ እና በተጨማሪም የአንድ አገር ዜጎች መብታቸውንና ግዴታቸውን በውል እንዲረዱ በማድረግ ንቁና ነፃ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መፍጠር ያስችላል በአጠቃላይ ማህበራዊ ተጠያቂነት የመንግስት አገልግሎት ከሙስና የፀዳና ውጤታማ እንዲሆን በማስቻል በአንድ አገር ውስጥ ሁለንተናዊ ልማት እንዲረጋገጥ የሚያደርግ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በውስጣቸው በሚያከናውኗቸው ስራዎች ራሳቸው ለማህበረሰቡ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሁኔታ በማረጋገጥ በዘርፉ አርኣያ ሁነው መገኘት የሚገባቸው መሆኑ አንስተው በዋናነት ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ማህበራዊ ተጠያቂነት በተደራጀ መንገድ እንዲተገበር ከፍተኛውን ሚና መጫዎት ይችላሉ፤ ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል፡፡

በማህበራዊ ተጠያቂነት በተለይም በታችኛው የአስተዳደር እርከን መንግስት ለህብረተሰቡ የሚያቀርባቸው እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ ወዘተ የመሳሰሉት መሰረታዊ አቅርቦቶች ከእቅድ ጀምሮ እስከ አፈፃፀም በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲፈፀሙ ለማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሳትፎ መደላድሎችን/መድረኮችን በመፍጠር፣ አቅምን በመገንባት፣ በተሳትፎ የሚገኙ ግኝቶች መፈፀማቸውን በመከታተል፣ አፈፃፀማቸው ላይ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ እና ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ በመሆን መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡: በመጨረሻም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በማህበራዊ ተጠያቂነት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ፣ በእቅዶቻቸውን ውስጥ በማካተትና ተገቢውን ሃብት በመመደብ ተግባራዊነቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ ተቋማችን የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮጀክት ላልፈፀሙ ሲማዶች በሁሉም ክልሎች ስልጠናዎች እየሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህ ስልጠና ፕሮግራም ስለማህበራዊ ተጠያቂነት ግንዛቤ የሚያዝበት ሲሆን ሲማዶች ይህንን እንደመነሻ በመውሰድ በራሳቸውን ማስፋትና መተግበር እንደሚችሉ ታሳቢ ተደርጓል በማለት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


13ኛው ክልል አቀፍ የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም በአርባ ምንጭ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበት ይህ የጋራ ፎረም በመንግስትና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከርና ችግሮችን በጋራ በመፍታት የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ ፎረም እንደሆነ በመርኃ ግብሩ ማስጀመሪያ ወቅት ተገልጿል፡፡ በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደተናገሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለአገር የሚያደርጉት አስተዋፅኦ እንዲጎለበት በፌዴራልና በክልል በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት ተገቢውን ድጋፋና ክትትል በማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በተለይም በፌዴራል ደረጃ የወጣው ህግ በየክልሎች በተሟላ መልኩ መተግበር ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቅንጅታዊ አሰራር መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ቅንጅታዊ አሰራር በመንግስትና በሲማዶች መካከል እንዲሁም እርስ በእርስ በሲማዶች መካከል ቀጣይነት ባለው መልኩ መተግበር ያለበት ነው፡፡ በዚሁ መሰረት በርካታ ክልሎች የGO-CSO Forum ያደራጁ ሲሆን ሲማዶችም ኔትወርኮችን በመፍጠር ለመቀናጀትና ለመተባበር ጥረቶችን ያደርጋሉ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዛሬው እለት የሚካሄደው የደቡብ ክልል GO-CSO Forum የዚሁ ቅንጅታዊ አሰራር አንድ አካል ሲሆን ክልሉ በሲማዶች ስራ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ ጠቃሚ መድረክ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በመጨረሻም ይህ ፎረም ከዓመት ዓመት ሳይቆራረጥ እንዲካሄድ የሚደረገው ጥረት የሚያስመሰግን ነው በማለት ለዚህም የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ይህንን ፎረም በማስቀጠሉ እንዲሁም በአጠቃላይ አዲሱን አዋጅ በሚገባ በመረዳት ከተቋማችን ጋር እንዲሁም በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ሲማዶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ለሚያደርገው ጥረት ላቅ ያለ ምስጋናዮን አቀርባለሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


በምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የተመራው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ቡድን በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚሰሩ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ተመለከተ፡፡

በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 ተመዝግበው በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ እና አርባ ምንጭ ከተማ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ሶስት ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎች በቦታው ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡ ጉብኝቱ በምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የተመራ ሲሆን በክልሉ የሚንቀሳቀሱትን ዩሪያዲስ ቪሌጅ ኢትዮጵያ (uriyadis village Ethiopia) ፤ ቦሳጆ የበጎ አድራጎት ድርጅትን (bosajo charity organization)፣ የቢላቭድ ኢትዮጵያ እንዲሁም አናሲሞስ ችልድረንስ ቪሌጅ ኢትዮጵያ የተባሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በህጻናትና ማህበረሰብ አቀፍ ልማት ላይ የሰሩትን ስራ ተመልክተዋል፡፡ ድርጅቶቹ በጎዳና ላይ የሚገኙ ህጻናትን በማንሳትና በመደገፍ እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመደገፍ የትምህርት፣ የጤናና እንክብካቤ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ በመስክ ምልከታው ለመረዳት ተችሏል፡፡


በተቋሙ አዘጋጅነት በሁሉም ክልሎች በማህበራዊ ተጠያቂነት ዙሪያ የሚሰጠው ስልጠና ተጀመረ፡፡

በማህበራዊ ተጠያቂነት ዙሪያ በአማራ ብሔራዊ ክልል ደብረታቦር ከተማ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ የስልጠናው ዓላማ ማህበራዊ ተጠያቂነትን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዘላቂነት በፕሮግራማቸው አካተው እንዲሰሩት ለማድረግ እና ጠያቂ እና ሃላፊነቱን የሚወጣ ማህበረሰብ ለመፍጠር ነው፡፡ በመርሃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ የሲማድ ዘርፍ ተወካይ አቶ ሙሉጌታ መኩሪያ ስልጠናውን ላዘጋጀው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምስጋናቸውን አቅርበው ከስልጠናው በኋላ በማህበራዊ ተጠያቂነት ዙሪያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የመንግስት አካላት ግንዛቤ በመያዝ ተግባራዊ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል፡፡በስልጠናው የማህበራዊ ተጠያቂነት ጽንሰ ሃሳብ፣በኢትዬጵያ አመጣጡን እና አተገባበር ዙሪያ እና በርካታ ርዕሰ ጉዳዬች ተነስተው ውይይት እየተደረገበት ሲሆን በቀጣይ በሁሉም ክልሎች ይሰጣል፡፡


የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ጎበኙ

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ያዘጋጀው የሚድያ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት  የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ተግባርና ሃላፊነት ለሚዲያ ተቋማት ግንዛቤ ማስያዝ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በአካል ማሳየት እና የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ ብሎም ማህበረሰቡ ስለድርጅቶቹ ግንዛቤ እንዲይዝና  በዚህ ሂደት የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀው ይህ የመስክ ምልከታ በተመረጡ አምስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፕሮጀክቶች ላይ የተደረገ ነው፡፡ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተሳባሰቡት ሃላፊዎቹ በትምህርት፣ በተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ፣ በህጻናት እንክብካቤና ድጋፍ እንዲሁም በውኃና ውኃ አቅርቦት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን ፕሮጀክቶች ፕሮጀክቶቹ  በሚከናወኑበት አካባቢ በመገኘት ተመልክተዋል፡፡ በሞጆ ከተማ በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በህጻናት እንክብካቤና ድጋፍ ላይ የሚሰራው ራፊቅ ፋውንዴሽንና በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራውን  ሴዳ (SEDA) የተባሉ ድርጅቶችን ፕሮጀክቶችን በማየት የጀመረው የመስክ ምልከታ በዝዋይ የክርስቲያን ኤድ ድርጅትን የውኃ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም በወንዶ ገነት የሚገኘውን የመና ህጻናትና የቤተሰብ መርጃ እና የህብረተሰብ ልማት ድርጅትን የተመለከተ ሲሆን የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የልማት ድርጅት በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ፣ በምስራቅ ሸዋ መቂና የመቂ ዙሪያ የሚገኙ ማህበረሰብ አቀፍ የልማት ስራዎችን ያካተተ ነው፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከፍተኛ የሪፎርም ስራ የተሰራበት ዘርፍ መሆኑን ለጉብኝት ተሳታፊዎች ገልጸው የሚድያ ተቋማት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለሀገር እያበረከተ ያለውን በጎ አስተዋጽዖ ለህዝብ እንዲያደርስና ድርጅቶችም የሚሰሩትን ስራ የሚድያ ሽፋን እንዲያገኙ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተቋሙ ከ4000 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተመዝገበው እንደሚገኙ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ከ2011 ጀምሮ ከ2000 በላይ አዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸውን አንስተው ባለስልጣኑ ድርጅቶችን ከመመዝገብ ባለፈ በትክክል መሬት ላይ ምን እየሰሩ ነው የሚለውን ሚዲያዎችና ማኅበረሰቡ ማወቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆኑን ለማሳየት የመስክ ጉብኝቱ በተቻለ መጠን አካታች እንዲሆን ጥረት አድርገናል ያሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት በቀጣይም በተለያየ አካባቢዎች በመዘዋወር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ለሚዲያዎችና ለህዝብ የማስተዋወቅ ስራዎችን አጠንክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ  እንዲመለከቱ በማድረጉ መደሰታቸውን ገልጸው ከሚድያ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠንከር ዘርፉን በሚገባ ማስተዋወቅና እንደዚህ ዓይነት የመስክ ምልከታዎችንም በማድረግ በሁሉም አካባቢ የሚሰሩ ድርጅቶችን ሚዲያዎች እንዲያውቋቸውና እንዲያግዟቸው ብታደርጉ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ባለስልጣኑ በሚሰራቸው የኮሚዩኒኬሽን ስራዎች ሁሉ አብሮ ለመስራትና የዘርፉን አበርክቶ ለህዝብ ለማድረስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የገለጹት የጉብኝቱ ተሳታፊዎች የዘርፉን አበርክቶ ለማህበረሰቡ ለማስተዋወቅ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ከጉብኝት መርኃ ግብሩ በተጨማሪ በተሳታፊዎች የተለያዩ ችግኞችን የመትከል መርኃ ግብር ተካሂዷል፡፡ ልዩ ልዩ የትምህርት፣ የህጻናት ድጋፍና እንክብካቤ፣ የውኃና የውኃ መሰረተ ልማት፣ ተፈጥሮ ኃብትና የአካባቢ ጥበቃ ላይ የተሰሩ ፕሮጀክቶች የታዩበት የመስክ ምልከታው ለሶስት ቀናት የተካሄደ ሲሆን በቀጣዩ በጀት ዓመት ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ አመራርና ባለሙያዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማና በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች የሚገኘውን The Pharos Foundation የመስክ ምልከታ ተደረገ፡፡

The Pharo Foundation የተባለው የውጭ ድርጅት እ.ኤ.አ በ2016 በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሰ ያለ ድርጅት ነው፡፡ በክልሉ እየተተገበረ ያለውን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመስክ የተመለከተ ሲሆን በዕለቱም ማስመረቅ ችሎዋል፡፡ ድርጅቱ በአሶሳ ከተማ Pharo Diagnostic የተሰኘውን የላብራቶሪ ማዕከል አስመርቋል፡፡ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናትና አመራሮች ተገኝተዋል፡፡ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በምረቃ ስነስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክ The Pharo Foundation የተሰኘው ድርጅት በአሶሳ ከተማ እና በክልሉ ወረዳዎች እያከናወናቸው የሚገኙትን በርካታ ፕሮጀክቶች መመልከት የቻልን ሲሆን በጤናው፣በግብርናው፣በትምህርት በንፁህ ውሃ አቅርቦት ላይ እየሰራ ያለው ስራ የሚያበረታታ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል ፡፡

ይህ ዛሬ የሚመረቀው Pharo Diagnostic center የላብራቶሪ ማዕከል ቀደም ሲል በክልሉ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ችግር የነበረበትን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ The Pharo Foundation በልማቱ ከሚያደርጋቸው አስተዋፅኦ ባሻገርም በሃገራችን በተከሰተው የተለያዩ ችግሮች ባደረግነው ሃገራዊ ጥሪ ድጋፍ ማድረጉን በማስታወስ የክልሉ መንግስትም ለሀገር በርካታ ስራዎችን ለሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል በማለት ባለስልጣን መስርያቤቱም ለነዚህ ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ድርጅቱ በክልላችን እንዲሁም በተለያዩ ወረዳዎች በጤናው፣በግብርናው ፣በትምህርት፣በንፁህ የመጠጥ ውሃ እና በመሳሰሉት በርካታ ስራዎችን እየሰራና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ያለ ድርጅት መሆኑን ከክልሉ ተወካዬች መረዳት ተችሏል፡፡ አያይዘውም ከዚህ ቀደም በክልሉ በጤናው ዘርፍ በርካታ ችግሮች ይስተዋሉ ነበረ ይህንን ችግር በክልሉ የማይገኙ የመመርመርያ ማሽኖችን ጨምሮ የጤና ዘርፍን ከፍ ሊያደርግ የሚችል የላብራቶሪ ማዕከል ማቋቋም ችሏል ብለዋል፡፡

.