የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተሳተፉበት ይህ የጋራ ፎረም በመንግስትና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከርና ችግሮችን በጋራ በመፍታት የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ ፎረም እንደሆነ በመርኃ ግብሩ ማስጀመሪያ ወቅት ተገልጿል፡፡ በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደተናገሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለአገር የሚያደርጉት አስተዋፅኦ እንዲጎለበት በፌዴራልና በክልል በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት ተገቢውን ድጋፋና ክትትል በማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በተለይም በፌዴራል ደረጃ የወጣው ህግ በየክልሎች በተሟላ መልኩ መተግበር ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቅንጅታዊ አሰራር መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ቅንጅታዊ አሰራር በመንግስትና በሲማዶች መካከል እንዲሁም እርስ በእርስ በሲማዶች መካከል ቀጣይነት ባለው መልኩ መተግበር ያለበት ነው፡፡ በዚሁ መሰረት በርካታ ክልሎች የGO-CSO Forum ያደራጁ ሲሆን ሲማዶችም ኔትወርኮችን በመፍጠር ለመቀናጀትና ለመተባበር ጥረቶችን ያደርጋሉ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዛሬው እለት የሚካሄደው የደቡብ ክልል GO-CSO Forum የዚሁ ቅንጅታዊ አሰራር አንድ አካል ሲሆን ክልሉ በሲማዶች ስራ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ ጠቃሚ መድረክ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በመጨረሻም ይህ ፎረም ከዓመት ዓመት ሳይቆራረጥ እንዲካሄድ የሚደረገው ጥረት የሚያስመሰግን ነው በማለት ለዚህም የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ይህንን ፎረም በማስቀጠሉ እንዲሁም በአጠቃላይ አዲሱን አዋጅ በሚገባ በመረዳት ከተቋማችን ጋር እንዲሁም በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ሲማዶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ለሚያደርገው ጥረት ላቅ ያለ ምስጋናዮን አቀርባለሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡