የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ያዘጋጀው የሚድያ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት  የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ተግባርና ሃላፊነት ለሚዲያ ተቋማት ግንዛቤ ማስያዝ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በአካል ማሳየት እና የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ ብሎም ማህበረሰቡ ስለድርጅቶቹ ግንዛቤ እንዲይዝና  በዚህ ሂደት የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀው ይህ የመስክ ምልከታ በተመረጡ አምስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፕሮጀክቶች ላይ የተደረገ ነው፡፡ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተሳባሰቡት ሃላፊዎቹ በትምህርት፣ በተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ፣ በህጻናት እንክብካቤና ድጋፍ እንዲሁም በውኃና ውኃ አቅርቦት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን ፕሮጀክቶች ፕሮጀክቶቹ  በሚከናወኑበት አካባቢ በመገኘት ተመልክተዋል፡፡ በሞጆ ከተማ በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በህጻናት እንክብካቤና ድጋፍ ላይ የሚሰራው ራፊቅ ፋውንዴሽንና በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራውን  ሴዳ (SEDA) የተባሉ ድርጅቶችን ፕሮጀክቶችን በማየት የጀመረው የመስክ ምልከታ በዝዋይ የክርስቲያን ኤድ ድርጅትን የውኃ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም በወንዶ ገነት የሚገኘውን የመና ህጻናትና የቤተሰብ መርጃ እና የህብረተሰብ ልማት ድርጅትን የተመለከተ ሲሆን የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የልማት ድርጅት በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ፣ በምስራቅ ሸዋ መቂና የመቂ ዙሪያ የሚገኙ ማህበረሰብ አቀፍ የልማት ስራዎችን ያካተተ ነው፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከፍተኛ የሪፎርም ስራ የተሰራበት ዘርፍ መሆኑን ለጉብኝት ተሳታፊዎች ገልጸው የሚድያ ተቋማት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለሀገር እያበረከተ ያለውን በጎ አስተዋጽዖ ለህዝብ እንዲያደርስና ድርጅቶችም የሚሰሩትን ስራ የሚድያ ሽፋን እንዲያገኙ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተቋሙ ከ4000 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተመዝገበው እንደሚገኙ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ከ2011 ጀምሮ ከ2000 በላይ አዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸውን አንስተው ባለስልጣኑ ድርጅቶችን ከመመዝገብ ባለፈ በትክክል መሬት ላይ ምን እየሰሩ ነው የሚለውን ሚዲያዎችና ማኅበረሰቡ ማወቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆኑን ለማሳየት የመስክ ጉብኝቱ በተቻለ መጠን አካታች እንዲሆን ጥረት አድርገናል ያሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት በቀጣይም በተለያየ አካባቢዎች በመዘዋወር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ለሚዲያዎችና ለህዝብ የማስተዋወቅ ስራዎችን አጠንክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ  እንዲመለከቱ በማድረጉ መደሰታቸውን ገልጸው ከሚድያ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠንከር ዘርፉን በሚገባ ማስተዋወቅና እንደዚህ ዓይነት የመስክ ምልከታዎችንም በማድረግ በሁሉም አካባቢ የሚሰሩ ድርጅቶችን ሚዲያዎች እንዲያውቋቸውና እንዲያግዟቸው ብታደርጉ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ባለስልጣኑ በሚሰራቸው የኮሚዩኒኬሽን ስራዎች ሁሉ አብሮ ለመስራትና የዘርፉን አበርክቶ ለህዝብ ለማድረስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የገለጹት የጉብኝቱ ተሳታፊዎች የዘርፉን አበርክቶ ለማህበረሰቡ ለማስተዋወቅ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ከጉብኝት መርኃ ግብሩ በተጨማሪ በተሳታፊዎች የተለያዩ ችግኞችን የመትከል መርኃ ግብር ተካሂዷል፡፡ ልዩ ልዩ የትምህርት፣ የህጻናት ድጋፍና እንክብካቤ፣ የውኃና የውኃ መሰረተ ልማት፣ ተፈጥሮ ኃብትና የአካባቢ ጥበቃ ላይ የተሰሩ ፕሮጀክቶች የታዩበት የመስክ ምልከታው ለሶስት ቀናት የተካሄደ ሲሆን በቀጣዩ በጀት ዓመት ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡