ፕሮግራሙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ካውንስል ጋር በጋራ በመሆን የተዘጋጀ ሲሆን ዝርዝር ሂደቱን በተመለከተ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እና የካውንስሉ ሃላፊ አቶ ሄኖክ መለሰ ማብራሪያ ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በመግለጫው በሰጡት ማብራሪያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ ጋር የጀመሩትን መልካም ግንኙነት አጠናክረው እንዲቀጥሉና መብትና ግዴታውን በውል የተረዳ፤በውይይት በምክንያታዊነት የሚያምን የነቃና በነጻነት የተደራጀ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተጀመሩ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ስራዎች ሊጠነክሩ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በተመሳሳይ የካውንስሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ ባስተላለፉት መልዕክት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ፕሮግራም ከመንግስት፣ከግሉ ዘርፍ እና ከብዙሃን መገናኛ ጋር ያላቸውን እና የሚኖራቸውን ግንኙነት ከምንግዜውም በበለጠ ከማጎልበቱም በላይ በጋራ ጉዳዬቻቸው ላይ በአንድነት ለመስራት ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ምክር ቤቱ በጽኑ ያምናል ብለዋል፡፡ ሃላፊዎቹ ሌሎች ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ባዛርና ኤግዚቪሽኑ ከሰኔ 23 አስከ 25 /2014 በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል የሚካሄድ ይሆናል፡፡