በሁሉም ክልሎች በሶሻል አካውንተብሊቲ ዙሪያ ስልጠና ለመስጠት የተያዘው እቅድ በደቡብ ፣በሲዳማ ፣ሐረር እና አፋር ክልሎች እየተተገበረ ይገኛል፡፡
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አርባ ምንጭ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመነሳት እንዲሁም ካላቸው ዘርፈ ብዙ ሃላፊነት በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ላይ የማህበራዊ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ የመሪነት ሚና መጫዎት የሚችሉ በመሆኑ በሁሉም ክልሎች ስልጠናው መዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡ ማህበራዊ ተጠያቂነት ሲባል ዜጎች በማንኛውም ደረጃ በሚገኝ የመንግስት አገልግሎት ገንቢ ተሳታፎ የሚያደርጉበት ሂደት ሲሆን በተሳትፎውም የመንግስት አገልግሎት ግልፅ፣ ተጠያቂነት ያለበት፣ ውጤታማ የሆነ፣መልካም አስተዳደርን በማስፈን የመንግስት አስተዳደር እንዲሻሻል እንደሚያደርግ እና በተጨማሪም የአንድ አገር ዜጎች መብታቸውንና ግዴታቸውን በውል እንዲረዱ በማድረግ ንቁና ነፃ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መፍጠር ያስችላል በአጠቃላይ ማህበራዊ ተጠያቂነት የመንግስት አገልግሎት ከሙስና የፀዳና ውጤታማ እንዲሆን በማስቻል በአንድ አገር ውስጥ ሁለንተናዊ ልማት እንዲረጋገጥ የሚያደርግ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በውስጣቸው በሚያከናውኗቸው ስራዎች ራሳቸው ለማህበረሰቡ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሁኔታ በማረጋገጥ በዘርፉ አርኣያ ሁነው መገኘት የሚገባቸው መሆኑ አንስተው በዋናነት ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ማህበራዊ ተጠያቂነት በተደራጀ መንገድ እንዲተገበር ከፍተኛውን ሚና መጫዎት ይችላሉ፤ ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል፡፡
በማህበራዊ ተጠያቂነት በተለይም በታችኛው የአስተዳደር እርከን መንግስት ለህብረተሰቡ የሚያቀርባቸው እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ ወዘተ የመሳሰሉት መሰረታዊ አቅርቦቶች ከእቅድ ጀምሮ እስከ አፈፃፀም በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲፈፀሙ ለማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሳትፎ መደላድሎችን/መድረኮችን በመፍጠር፣ አቅምን በመገንባት፣ በተሳትፎ የሚገኙ ግኝቶች መፈፀማቸውን በመከታተል፣ አፈፃፀማቸው ላይ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ እና ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ በመሆን መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡: በመጨረሻም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በማህበራዊ ተጠያቂነት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ፣ በእቅዶቻቸውን ውስጥ በማካተትና ተገቢውን ሃብት በመመደብ ተግባራዊነቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ ተቋማችን የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮጀክት ላልፈፀሙ ሲማዶች በሁሉም ክልሎች ስልጠናዎች እየሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህ ስልጠና ፕሮግራም ስለማህበራዊ ተጠያቂነት ግንዛቤ የሚያዝበት ሲሆን ሲማዶች ይህንን እንደመነሻ በመውሰድ በራሳቸውን ማስፋትና መተግበር እንደሚችሉ ታሳቢ ተደርጓል በማለት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡