በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 አንቀጽ 86 መሰረት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሚተዳደር የሲቪል ማህበረሰብ ፈንድ እንደሚቋቋም ተደንግጓል፡፡ ባለስልጣን መስሪያቤቱም ይህንኑ በሚመለከት ባወጣው ‹‹የሲቪል ማህበረሰብ ፈንድ አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 848/2014 መሰረት ለሃገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፈንዱ ድጋፍ ለማድረግ በቀን 10/06/2014 ዓ.ም ግልጽ ፕሮፖዛል መቀበያ ጥሪ ማስታወቂያ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያወጣ ሲሆን በጥሪው ማስታወቂያ መሰረት 95 /ዘጠና አምስት/ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለውድድር ቀርበው በመመዝገብ በቅድመ ምዘና እና ቴክኒክ ኮሚቴው ውሳኔ መሰረት ሶስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመረጣቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት ዛሬ በውድድሩ አሸናፊ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር የድርጅቶቹን እና የተቋሙን ተግባርና ሃላፊነት የያዘ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ ፈንዱ በሁለት ዙር የሚለቀቅ ሲሆን የመጀመሪያዎቹን ሶስት ወራት በመመልከት የሚቀጥለው 50 ፐርሰንት የሚለቀቅ መሆኑ በስምምነት ስነ ስርዓቱ ላዩ ተገልጿል፡፡ በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ ድርጅቶች በሰጡት አስተያየት ሌሎች ሃገራት ላይ ያለ ልምድ መወሰዱ ፣የውድድር ሂደቱ ግልጽ መሆኑ አበረታች ነው በማለት ተቋሙ የሰጠንን ሃላፊነት ሙሉ በሙሉ ለመወጣት እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡