የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የመማክርት ጉባኤ ተመሰረተ::



ባለስልጣኑ ካሪታስ ሲዊዘርላንድ (CARITAS Switzerland) ከተባለ የሲዊዘርላንድ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ካሪታስ ሲዊዘርላንድ (CARITAS Switzerland) በኢትዮጵያ ቀጠናዊ ቢሮ ለመክፈት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በስምምነቱ ወቅት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት አዲስ አበባ የበርካታ ቀጠናዊና አለም ዓቀፋዊ ተቋማት መቀመጫ መሆንዋን ጠቁመው ካሪታስ ሲዊዘርላንድ (CARITAS Switzerland) የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ቢሮውን ለመክፈት በመምጣቱ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ካለምንም ተጽዕኖ ነጻ ሆነው መንቀሳቀስ እንዲችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው ይህንን አጋጣሚ በመጠቀምም ሪጅናል ቢሯቸውን ወደ ኢትዮጵያ እያዞሩ ያሉ ድርጅቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ በሰሜን የኢትዮጵያ ከፍል እንዲሁም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በጦርነቱና በከፍተኛ ድርቅ ዜጎች ችግር ላይ ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ እንደካሪተስ ያሉ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቀነስ ትልቅ ሚና የሚኖራቸው በመሆኑ የምስራቅ አፍሪካ ሪጅናል ቢሮ በአዲስ አበባ ለመክፈት መነሳታቸው የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡

የካሪታስ ሲዊዘርላንድ (CARITAS Switzerland) የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ሚስተር ያንሲ በበኩላቸው ድርጅታቸው በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል እና በኦሮሚያ ክልል በርካታ የሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደቆየ ጠቁመው ስምምነቱ ድርጅታቸው ማዕከሉን አዲስ አበባ አድርጎ የሰብዓዊ ድጋፎቹን በተቀላጠፈ መልኩ በሚንቀሳቀስባቸው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለማዳረስ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርላቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ካሪታስ ሲዊዘርላንድ (CARITAS Switzerland) በስዊዘርላንድ ሀገር ከተመሰረተ 45 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በኢትዮጵያ በአዲሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሰ ያለና በአሁኑ ወቅትም ከ10 በላይ በሚሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ በአፍሪካ፣ በኢስያ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በአውሮፓ እንዲሁም አሜሪካ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ የስምምነት ሰነድ የምስራቅ አፍሪካ ሪጅናል ቢሮውን በአዲስ አበባ ለመክፈት የሚያስችለው ነው፡፡
ዓመታዊ ሪፖርት በወቅቱ በማያስገቡ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ብሎም በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ዙሪያ በተለያየ መልኩ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ፍቃድ መውሰድ እንዳለባቸው ተገለጸ
ዓመታዊ ሪፖርት በወቅቱ በማያስገቡ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ብሎም በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ዙሪያ በተለያየ መልኩ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ፍቃድ መውሰድ እንዳለባቸው ተገለጸ ፡፡ ተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸሙን በማኔጅመንት ደረጃ ገምግሟል፡፡ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ዙሪያ በተለያየ መልኩ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከባለስልጣን መስሪያቤቱ ፍቃድ ሳይወስዱ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችሉ የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በግምገማው ወቅት ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 መሰረት ድርጅቶች ህልውናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ገልጸው ይህንን መሰረት በማድረግ በርካታ ድርጅቶች ለተቋሙ ሪፖርት ማድረጋቸውን ነገር ግን የተወሰኑ ድርጅቶች ወቅቱን ጠብቀው ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ያላስገቡ በመሆኑ ይህንን ተፈጻሚ ባላደረጉ ድርጅቶች ላይ ተቋሙ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ማስጀመር፣የዜጎች ቻርተር ተግባራዊ ማድረግ፣ደንቡ ጸድቆ ወደ ስራ ማስገባት፣የመማክርት ጉባኤን መመስረት፣እቅድ መከለስ እና ስልጠናን ወደ ተግባር መቀየር የቀጣይ 6 ወራት የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም አመራሩ ከደራሽ ስራ ወጥቶ ስትራቴጂክ የሆኑ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የአመራርነት ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡



ወ/ሮ ቃልኪካዳን መንግስቴ የእቅድ በጀትና ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የተቋሙን የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት አፈጻጸም ፣ያጋጠሙ ችግሮች፣የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን ያካተተ ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡: በአፈጻጸሙ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ የተጀመሩ የሃብት አሰባሰብ ስራዎች ፣ለድርጅቶች ግብረመልስ የመስጠት ስራ መጀመሩ፣ የበጎ አድራጊነትና በጎፍቃደኝነት ባህልን ከማጎልበት አንጻር የተሰሩ የንቅናቄ ስራዎች፣ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሰራሮች እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት በእቅድ እና አፈጻጸም ላይ እንዲወያዩ መደረጉ በአፈጻጸሙ የታዩ ጠንካራ ጎኖች ሲሆኑ በወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታ ምክንያት የአዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባ መቀነስ፣የሰነድ ማረጋገጥ ስራ ያለማስጀመር እና ሌሎችም መሻሻል የሚገባቸው ተግባራት መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜና ባለስልጣኑ ሰርቭ ግሎባል ከተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሰርቭ ግሎባል ጋር በመተባበር በጎ ፍቃደኛ ፈላጊና፤ በጎ ፍቃድ ስራ ላይ ለመሰማራት የተመዘገቡ አካላትን የሚያገናኝ Voluntarism management information system ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡ ሲስተሙ ማንኛውም አካል በሙያው በበጎ ፍቃደኝነት ማገልገል ሲፈልግ በኦንላይን የሚመዘገብበት ሲሆን በቀላሉ ተመዝጋቢዎችን እና በጎ ፍቃደኞችን የሚፈልጉ ተቋማትን የሚያገናኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች እድል ከሰጠናቸውና ሁኔታዎችን ካመቻቸን ለአገራችን እድገትና ብልፅግና ትልቅ ሚና አላቸው፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሴቶች ማኅበር ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር አዲስ ለተቀጠሩ ሰራተኞች በአካል ጉዳተኛ ሴቶች አካታችነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡ በስልጠናው ላይ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማኅበር ስራ አሲኪያጅ ወ/ሮ ድባቤ ባጫ እንዳሉት ማኅበሩ ከተመሰረተ ሃያ ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን በአሁን ሰዓት በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም በዋናነት ማኅበሩ የሚሰራቸው ስራዎች የአቅም ግንባታ ስጠናዎች፣ የገቢ ማስገኛ ስራዎች፣በመብትና ጥቅሞች ላይ እየሰራ እንደሆነ በመግለፅ ይህ ስልጠና ያስፈለገው በአካል ጉዳተኛ ሴቶች አካታችነት ላይ ለባለስልጣኑ ሰራተኞች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡



በክብር እንግድነት የተገኙት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት አዲሱ አዋጅ 1113/2011 ለአካል ጉዳተኞች ሰፊ እድል የሰጣቸው ሲሆን በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቦርድ ውስጥ ያላቸው ውክልና ከፍ ያለ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አክለውም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማንኛውንም ስራ ሲሰሩ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካቶ መስራት እንዳለባቸው በማንሳት እንዲሁም መመሪያዎችም ሆኑ ህጎች ሲዘጋጁ አካል ጉዳተኞችን ባካተተ መልኩ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ሌላው ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለአካል ጉዳተኞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ ሲሆን ለአገር ልማትና እድገት ለማምጣት ለሚሰሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ባዘጋጀው የክትትልና ግምገማ ማንዋል ላይ የማስተዋወቂያ መርኃ ግብር ተካሄደ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባዘጋጀው የክትትልና ግምገማ ማንዋል ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረቶች በተገኙበት የማስተዋወቂያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡ በማስተዋወቂያ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንዳሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር ብልጽግናና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ድጋፋዊ የሆነ የክትትልና የግምገማ ስርዓትን በመዘርጋት ቀልጣፋና ተገማች የሆነ አሰራርን ለመዘርጋት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡



ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዘርፉ ላይ የመንግስት አማካሪ እንደመሆኑ መጠን በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ያስፈልገዋል፡፡ ስለሆነም የክትትልና የግምገማ ስርዓታችንን ማስተካከልና ማዘመን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ አክለውም በዚህ የክትትልና የግምገማ ማንዋል መሰረት ለድርጅቶች ደረጃ የሚሰጥ ሲሆን ዘርፉ በሀገሪቱ GDP ላይ ያለው አበርክቶ ለመለየት ትልቅ ሚና ስለሚኖረው በዘፈቀደ ከሚወሰኑ ውሳኔዎችም የሚታደግ ነው ብለዋል፡፡
3ተኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የፌዴራልና ክልል ባለድርሻ የመንግስት ተቋማት የጋራ ጉባኤ ተሳታፊዎች የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎበኙ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩ ወልዴ በገለጻቸው የስራ እድል ፈጠራ፣የቴክኖሎጂ ሽግግር፣የውጭ ምንዛሬ እና ግብርናን ማዘመን የኢንደስትሪ ፓርኩ አራት መሰረታዊ ጥቅሞች እንደሆኑ ለጎብኚዎች አስረድተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው የሲዳማ ብ/ክ/መንግስትን እንደዚህ አይነት የጉብኝት መርሃ ግብር በማዘጋጀት ተሳታፊዎቹ የልማት ስራዎችን እንዲመለከቱ በማድረጋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ጎብኚዎቹም ባዩት ነገር እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
3ተኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የፌዴራልና ክልል ባለድርሻ የመንግስት ተቋማት የጋራ ጉባኤ በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ በርካታ የክልል እና የፌዴራል የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት እና የኢትዬጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የኢፌዴሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዬን ጢሞቲዬስ ባስተላለፉት መልዕክት በባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት ልዩ አጽንኦት በመስጠት ህጉን ማሻሻል መቻሉን ገልጸው በአንድ ሃገር የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተዋናዬች በተጨማሪ ያለትርፍ ለበጎ አድራጎት ተግባር ተሰባስበው እና ተደራጅተው የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ሃገራዊ ሁኔታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ሲገልጹ በሃገሪቱ በግጭት ምክንያት የወደሙ መሰረተ ልማቶችና ንብረቶችን ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ መልሶ የመገንባት፣ቁሳዊ ያልሆነውን የወንድማማችነትና አብሮነት በተመለከተ እርቅ ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንዲሁም እንደዚህ ዓይነት የግጭት ምንጭ የሆኑ ጉዳዬችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠት የተቋቋመውን የሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሚጠራው የውይይት መድረኮች ላይ ተሳታፊ መሆን እና የማገዝ ስራ መስራት እንደሚገባ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡



የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት የምክክር መድረኩ ዓላማ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የተከናወኑ ዐበይት ሥራዎችን በመገምገም፣ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ማረም፤ ማጽናትና ማላቅ በሚገቡን ጉዳዮችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ጉባኤው ተወያይቶ ማስቀመጥ ብሎም በዘርፉ ሚታዩ ክፍተቶችንም በመለየት የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥና ምርጥ ተሞክሮዎችን መለዋወጥም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተፈጠረው ችግር በርካታ ችግሮች የደረሱ መሆኑን ገልጸው ይህንን ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውንና በከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙትን ወገኖቻችን መደገፍ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ቢሆንም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከዚህ አንጻር ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰብዓዊ ዕርዳታና ድጋፍ በማሰባሰብ “እኔም ለወገኔ” በሚል ከቀዬቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ድጋፍ የሚውል ሀብት በማሰባሰብና በቦታው በማድረስ ጭምር ያደረጉት ርብርብና አሁንም በማድረግ ላይ የሚገኙት ድርጅቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከመንግስት ጎን በመቆም ሀገርን ከአደጋ ለመታደግ ያሳዩት ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ለሲዳማ ብ/ክ/መንግስት እዲሁም ወጪውን በመሸፈን ተባባሪ ለሆነው CSSP2 ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የተቋሙ ሰራተኞች በሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ በመገኘት የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰበሰቡ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ በመገኘት ወራሪውን የትግራይ ቡድን ለመመከት በግንባር ሲዋደቁ የነበሩ አርሶ አደር ዘማቾችን ሰብል ሰብስበዋል፡፡ በዚህ የሰብል ስብሰባ መርሃ ግብር ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላን ጨምሮ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪና የወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ ወራሪው ቡድን በርካታ ወንጀሎችን ሲሰራ ቆይቷል፤ እኛም ስንመክት ቆይተናል ያሉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ፤ ይህ ወራሪ ቡድን የቃጣብንን ጥቃት መላው ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመነቃነቅና በጋራ በመሆን ከወረራቸው የአፋርና የአማራ ክልሎች ተጠራርጎ እንዲወጣ በማድረግ ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርገዋል ብለዋል፡፡ ማክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም አሸባሪ ቡድኑ ዳግም እንዳይነሳና መልሶ ወረራ እንዳይፈጽም እስከወዲያኛው የማጥፋት ስራ በመንግስት በቀጣይ የሚሰራበት መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብለው የሚያስቡ የውስጥም የውጪ ጠላቶችን ያሳፈረ፤ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የማትፈርስ ሀገር መሆኗንና የትኛውም ችግር ቢመጣ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግሮቻቸውን ወደጎን በመተው ለጋራ አላማቸው የሚሰለፉ መሆናቸውን ያስመሰከሩበት ድል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡



የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በንግግራቸው እንደገለጹት አጋጣሚው ኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ግንኙነታችንን እንድናጠናክር እድል ሰጥቶናል፤ በርካታ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች አሉብን፤ ጥቃቅን የሆኑትን የዘርና መሰል የሆኑ ልዩነቶቻችንን ትተን በጋራ ከሰራን ፖለቲካውንም ኢኮኖሚውንም እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብራችንን ማስተካከል የምንችል መሆኑን ያየንበት ነው፡፡ ጠላቶቻችን እርስ በርስ ይበላላሉ፤ ይጫረሳሉ ብለው ለ30 አመታት የሰሩልንን የልዩነት ግንብ ትተን የአንድነት ግንብ የሰራንበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ይህን ጦርነት ለመመከት ግንባር ድረስ በመዝመት ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርጉ የነበሩትን የሞረትና ጅሩ ወረዳ ሚሊሻዎችን ሰብል ለመሰብሰብ ከመሃል አዲስ አበባ ድረስ ስንመጣ አንድ መሆናችንን፤ የእናንተ ጉዳት የእኛም ጉዳት ነው ለማለትና ሁልም ቢሆን ኢትዮጵያውያን ከጎናችሁ ነን ለማለት ነው፡፡የወደመውን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድቀቶችን የማስተካከል ብዙ የቤት ስራዎች ይጠበቁብናል፡፡ጦርነቱ አሁን ባለበት ሁነኔታ የኛ መፈክር ሊሆን የሚገባው እናልማ፣እንገንባ፣ እንዘጋጅ ነው፡፡ ኢኮኖሚያችንን መልሶ ለመገንባት መረባረብ ያለብን ወቅት ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ዛሬ መጥተን እንዳየነው በሚያስደንቅ ሁኔታ አደለም ይህን ወረዳና ዞን ድፍን ኢትዮጵያን መመገብ የሚችል ትልቅ የእርሻ አቅም ያለው መሆኑን አይተናል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ የግብርና ምርታችን አመርቂ የሚባል ነው፡፡ የወደሙ ከተሞችን መልሶ በመገንባትም ከፍተኛ ርብርብ ማድርግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው፡፡ ዛሬ እዚህ የተገኘንበት አንዱና ትልቁ ምክንያትም ለእኛ ሲሉ ነው ግንባር ድረስ ዘምተው የቆሰሉት፣ የተጎዱት፣ ብለን ህመማቸው ህምማችን ቁስላቸው ቁስላችን መሆኑን ለመግለጽ ስንመጣ ሀብታቸውን በመሰብሰብ ኢኮኖሚያቸው ወደተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል የበኩላችንን አስተዋጽዖ እያበረከትን ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ ጦርነቱ ገና ነው አላለቀም፡፡ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በላይ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ጠላት የማይበገር ሰራዊት መገንባት፤ ስለሰላም እየሰበኩ ጎን ለጎን መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ አንድነታችንን እናጠናክር ለዚህም ነው ወደዚህ የመጣነው፡፡የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በስሩ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን በማስተባበር በአንድ ቀን ጥሪ ብቻ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ ለተጎጂ ወገኖቻችን አሰባስበናል፤ በቀጥታም ለተጎጂዎች እንዲደርስም እያደረግን ነው፡፡ ለተቋሙ ሰራተኞች በቢሮ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ ብዙ መንገድ አቋርጣችሁ ለዘማቾቹ አለን ከጎናችሁ ነን በማለታችሁ እጅግ የከበረ ምስጋናየን አቀርባልሁ ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸል፡፡

የሞረትና ጅሩ ወረዳ ዋና አስተዳዳ አቶ ሙሉጌታ በበኩላቸው ወረዳው በስንዴና በጤፍ እንዲሁም በጥራጥሬ ሰብሎች በምስርና በባቄላ የሚታወቅ መሆኑን ጠቁመው ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩም የአካባቢውን የሰብል ሀብት መጥተው የጎበኙት እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ወራሪው የህውኃት ቡድን ይህን አካባቢ ለማጥፋት አጎራባች ወረዳዎች ድረስ ተጠግቶ ነበር ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በመላው ኢትዮጵያውያን ርብርብ ወደመጣበት እንዲመለስ ተደርጓል ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ይህ አካባቢ መደገፍ ይገባዋል ብላችሁ ብዙ ኪሎሜትር አቋርጣችሁ በመምጣታችሁ እንዲሁም ሰራተኛ ጭምር ቀጥራችሁ የዘማቾችን ስለሰበሰባችሁና ድጋፍ ስላደረጋችሁልን ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለሁለተኛ ጊዜ ባደረገው በዚህ የሰብል መሰብሰብ መርኃ ግብር ከ3.5 ሄክታር በላይ በስንዴና በጤፍ የተሸፈነ ሰብል የተሰበሰበ ሲሆን በወረዳው ለችግር ለተዳረጉ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ይሆን ዘንድ የተለያዩ አልባሳትንም ለወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ አስረክበዋል፡፡
ዶክተርስ ዊዝ አፍሪካ ኩኣም እና እዩ ኢትዮጵያ የተባሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች የመድኃኒት ድጋፍ አደረጉ፡፡
ዶክተርስ ዊዝ አፍሪካ ኩኣም እና እዩ ኢትዮጵያ የተባሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ከ754 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የመድኃኒት ድጋፍ አድርገዋል፡፡በባሕር ዳር ተገኝተው ድጋፉን ያስረከቡት የዶክተርስ ዊዝ አፍሪካ ኩኣም የፕሮግራም ኀላፊ ዶክተር አደም ፀጋዬ ድርጅታቸው ያደረገው ድጋፍ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ በመገንባት እና ሥራ ለማስጀመር ድርጅታቸው የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡ የዶክተርስ ዊዝ አፍሪካ ኩኣም ፕሮግራም በጤናው ዘርፍ በጠረፍ አካባቢዎች ላይ እየሠራ ያለ ድርጅት መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡



ድርጅቶችን በማስተባበር ድጋፍ እያሠባሰቡ የሚገኙት የኢፌድሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የከፋ ሰብዓዊ፣ አካላዊ እና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል ብለዋል፡፡ ውድመቱ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ይሁን እንጅ ጉዳቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መልሶ ለመገንባት የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ የተመዘገቡ 3 ሺህ 500 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አሉ ያሉት አቶ ፋሲካው እነዚህ ድርጅቶች በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት 142 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል ነው ያሉት፡፡ በገቡት ቃል መሠረት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሌሎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከእዩ ኢትዮጵያ ድጋፍ ይዘው የመጡት ታሪኩ ወንዴ ድርጅታቸው 175 ሽህ ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ድጋፉ ተቋማቱን አገልግሎት እንዲሰጡ ያግዛል ብለዋል፡፡ ሌሎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘገባው የአማራ ሚድያ ኮርፖሬሽን ነው፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሃዋሳ ከተማ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት ስልጠና ሰጠ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሃዋሳ ከተማ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን DEC ከተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጀው ነው፡፡ በስልጠናው ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጨምሮ በሲዳማ ክልል የሚገኙ ባለድርሻ የመንግስት ተወካዮችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡: የስልጠናው ዋነኛ አላማ በመንግስት ተቋማት፣ በግልና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበጎ ፈቃድና የበጎ አድራጊነት ተግባራትን በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ ለመምራት እንዲረዳ በባለስልጣኑ የተዘጋጀውን `volunteerism promotion and management guidance note ለማስተዋወቅና ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታልሞ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ተቋማዊ አሰራር ለመፍጠር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ለማድረግ የሚያስችል ዓይነተኛ ዓላማ ያለው ስልጠና እንደሆነ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡



የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ጂማ ዲልቦ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንዳሉት አንድነታችንን፣ አብሮነታችንን ለማጠናከር የበጎ ፈቃደኝነትና የበጎ አድራጊነት ባህል እጅጉን አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ እንደሀገር ያጋጠሙንን ችግሮች ለመፍታት መነጋገር፣ መግባባት አንዳችን ለሌላችን መልካም ማድረግ አለብን፤ ለምናስበው ልማትና ብልፅግና እንዲሁም አሁን ከገባንበት ውጥንቅጥ ለመውጣት የበጎ ፈቃደኝነትና የበጎ አድራጊነት እሳቤ እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የበጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነት እሳቤ እንክብካቤ የሚሻ በመሆኑ መንከባከብና ማሳደግ ተገቢ ነው ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልፀዋል፡፡ የበጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነት በኢትዮጵያ ባህል አልሆነም፤ በዘመቻ መልክ የሚከናወን በመሆኑም ለሀገሪቱ ያለው አበርክቶ ምን ያህል እንደሆነ በትክክል አይታወቅም፡፡ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን የመሰነድ ባህል ባለመኖሩ በበጎ ፈቃድ የተከናወኑ ተግባራት ምን ያህል እንደሆኑና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፤ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ዘርፍ ያበረከተው አስተዋፅዖ የሚታወቅና በስርዓት የሚመራ አይደለም፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን በመረዳት ዘርፉ በስርዓት ይመራ ዘንድ ያለውንም አበርክቶ በትክክል ለማመላከትና ለማስተካከል እየሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ አራርሶ ገረመው በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሲዳማ ክልል ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት እንዲህ አይነት ስልጠና ማዘጋጀቱ እንዳስደሰታቸው ጠቁመው እንደ ክልል የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በመዋቅር ደረጃ እስከታች ድረስ በመዘርጋት ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል፡፡ አያይዘውም ጋይድ ላይኑን በሲዳምኛ ለማስተርጎም ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን አንስተው ማህበረሰባችን ጥልቅ የሆነ የበጎ ፈቃድ ባህል ያለው በመሆኑ ይህን ከልብ በሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡







