የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሃዋሳ ከተማ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን DEC ከተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጀው ነው፡፡ በስልጠናው ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጨምሮ በሲዳማ ክልል የሚገኙ ባለድርሻ የመንግስት ተወካዮችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡: የስልጠናው ዋነኛ አላማ በመንግስት ተቋማት፣ በግልና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበጎ ፈቃድና የበጎ አድራጊነት ተግባራትን በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ ለመምራት እንዲረዳ በባለስልጣኑ የተዘጋጀውን `volunteerism promotion and management guidance note ለማስተዋወቅና ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታልሞ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ተቋማዊ አሰራር ለመፍጠር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ለማድረግ የሚያስችል ዓይነተኛ ዓላማ ያለው ስልጠና እንደሆነ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ጂማ ዲልቦ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንዳሉት አንድነታችንን፣ አብሮነታችንን ለማጠናከር የበጎ ፈቃደኝነትና የበጎ አድራጊነት ባህል እጅጉን አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ እንደሀገር ያጋጠሙንን ችግሮች ለመፍታት መነጋገር፣ መግባባት አንዳችን ለሌላችን መልካም ማድረግ አለብን፤ ለምናስበው ልማትና ብልፅግና እንዲሁም አሁን ከገባንበት ውጥንቅጥ ለመውጣት የበጎ ፈቃደኝነትና የበጎ አድራጊነት እሳቤ እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የበጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነት እሳቤ እንክብካቤ የሚሻ በመሆኑ መንከባከብና ማሳደግ ተገቢ ነው ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልፀዋል፡፡ የበጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነት በኢትዮጵያ ባህል አልሆነም፤ በዘመቻ መልክ የሚከናወን በመሆኑም ለሀገሪቱ ያለው አበርክቶ ምን ያህል እንደሆነ በትክክል አይታወቅም፡፡ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን የመሰነድ ባህል ባለመኖሩ በበጎ ፈቃድ የተከናወኑ ተግባራት ምን ያህል እንደሆኑና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፤ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ዘርፍ ያበረከተው አስተዋፅዖ የሚታወቅና በስርዓት የሚመራ አይደለም፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን በመረዳት ዘርፉ በስርዓት ይመራ ዘንድ ያለውንም አበርክቶ በትክክል ለማመላከትና ለማስተካከል እየሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ አራርሶ ገረመው በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሲዳማ ክልል ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት እንዲህ አይነት ስልጠና ማዘጋጀቱ እንዳስደሰታቸው ጠቁመው እንደ ክልል የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በመዋቅር ደረጃ እስከታች ድረስ በመዘርጋት ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል፡፡ አያይዘውም ጋይድ ላይኑን በሲዳምኛ ለማስተርጎም ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን አንስተው ማህበረሰባችን ጥልቅ የሆነ የበጎ ፈቃድ ባህል ያለው በመሆኑ ይህን ከልብ በሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡