ዓመታዊ ሪፖርት በወቅቱ በማያስገቡ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ብሎም በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ዙሪያ በተለያየ መልኩ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ፍቃድ መውሰድ እንዳለባቸው ተገለጸ ፡፡ ተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸሙን በማኔጅመንት ደረጃ  ገምግሟል፡፡ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ዙሪያ በተለያየ መልኩ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ እያሰባሰቡ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከባለስልጣን መስሪያቤቱ ፍቃድ ሳይወስዱ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችሉ የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በግምገማው ወቅት ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 መሰረት ድርጅቶች ህልውናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ገልጸው ይህንን መሰረት በማድረግ በርካታ ድርጅቶች ለተቋሙ ሪፖርት ማድረጋቸውን ነገር ግን የተወሰኑ ድርጅቶች ወቅቱን ጠብቀው ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ያላስገቡ በመሆኑ ይህንን ተፈጻሚ ባላደረጉ ድርጅቶች ላይ ተቋሙ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት ማስጀመር፣የዜጎች ቻርተር ተግባራዊ ማድረግ፣ደንቡ ጸድቆ ወደ ስራ ማስገባት፣የመማክርት ጉባኤን መመስረት፣እቅድ መከለስ እና ስልጠናን ወደ ተግባር መቀየር የቀጣይ 6 ወራት የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም አመራሩ ከደራሽ ስራ ወጥቶ ስትራቴጂክ የሆኑ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የአመራርነት ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ቃልኪካዳን መንግስቴ የእቅድ በጀትና ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የተቋሙን የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት አፈጻጸም ፣ያጋጠሙ ችግሮች፣የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን ያካተተ ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡: በአፈጻጸሙ በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ የተጀመሩ የሃብት አሰባሰብ ስራዎች ፣ለድርጅቶች ግብረመልስ የመስጠት ስራ መጀመሩ፣ የበጎ አድራጊነትና በጎፍቃደኝነት ባህልን ከማጎልበት አንጻር የተሰሩ የንቅናቄ ስራዎች፣ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ ቅንጅታዊ አሰራሮች እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት በእቅድ እና አፈጻጸም ላይ እንዲወያዩ መደረጉ በአፈጻጸሙ የታዩ ጠንካራ ጎኖች ሲሆኑ በወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታ ምክንያት የአዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባ መቀነስ፣የሰነድ ማረጋገጥ ስራ ያለማስጀመር እና ሌሎችም መሻሻል የሚገባቸው ተግባራት መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜና ባለስልጣኑ ሰርቭ ግሎባል ከተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሰርቭ ግሎባል ጋር በመተባበር በጎ ፍቃደኛ ፈላጊና፤ በጎ ፍቃድ ስራ ላይ ለመሰማራት የተመዘገቡ አካላትን የሚያገናኝ Voluntarism management information system ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡ ሲስተሙ ማንኛውም አካል በሙያው በበጎ ፍቃደኝነት ማገልገል ሲፈልግ በኦንላይን የሚመዘገብበት ሲሆን በቀላሉ ተመዝጋቢዎችን እና በጎ ፍቃደኞችን የሚፈልጉ ተቋማትን የሚያገናኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡