ዶክተርስ ዊዝ አፍሪካ ኩኣም እና እዩ ኢትዮጵያ የተባሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ከ754 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የመድኃኒት ድጋፍ አድርገዋል፡፡በባሕር ዳር ተገኝተው ድጋፉን ያስረከቡት የዶክተርስ ዊዝ አፍሪካ ኩኣም የፕሮግራም ኀላፊ ዶክተር አደም ፀጋዬ ድርጅታቸው ያደረገው ድጋፍ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ በመገንባት እና ሥራ ለማስጀመር ድርጅታቸው የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡ የዶክተርስ ዊዝ አፍሪካ ኩኣም ፕሮግራም በጤናው ዘርፍ በጠረፍ አካባቢዎች ላይ እየሠራ ያለ ድርጅት መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

ድርጅቶችን በማስተባበር ድጋፍ እያሠባሰቡ የሚገኙት የኢፌድሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የከፋ ሰብዓዊ፣ አካላዊ እና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል ብለዋል፡፡ ውድመቱ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ይሁን እንጅ ጉዳቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መልሶ ለመገንባት የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ የተመዘገቡ 3 ሺህ 500 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አሉ ያሉት አቶ ፋሲካው እነዚህ ድርጅቶች በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት 142 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል ነው ያሉት፡፡ በገቡት ቃል መሠረት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሌሎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከእዩ ኢትዮጵያ ድጋፍ ይዘው የመጡት ታሪኩ ወንዴ ድርጅታቸው 175 ሽህ ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ድጋፉ ተቋማቱን አገልግሎት እንዲሰጡ ያግዛል ብለዋል፡፡ ሌሎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘገባው የአማራ ሚድያ ኮርፖሬሽን ነው፡፡