ካሪታስ ሲዊዘርላንድ (CARITAS Switzerland) በኢትዮጵያ ቀጠናዊ ቢሮ ለመክፈት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በስምምነቱ ወቅት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት አዲስ አበባ የበርካታ ቀጠናዊና አለም ዓቀፋዊ ተቋማት መቀመጫ መሆንዋን ጠቁመው ካሪታስ ሲዊዘርላንድ (CARITAS Switzerland) የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ቢሮውን ለመክፈት በመምጣቱ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ካለምንም ተጽዕኖ ነጻ ሆነው መንቀሳቀስ እንዲችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው ይህንን አጋጣሚ በመጠቀምም ሪጅናል ቢሯቸውን ወደ ኢትዮጵያ እያዞሩ ያሉ ድርጅቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ በሰሜን የኢትዮጵያ ከፍል እንዲሁም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በጦርነቱና በከፍተኛ ድርቅ ዜጎች ችግር ላይ ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ እንደካሪተስ ያሉ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቀነስ ትልቅ ሚና የሚኖራቸው በመሆኑ የምስራቅ አፍሪካ ሪጅናል ቢሮ በአዲስ አበባ ለመክፈት መነሳታቸው የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡

የካሪታስ ሲዊዘርላንድ (CARITAS Switzerland) የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ሚስተር ያንሲ በበኩላቸው ድርጅታቸው በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል እና በኦሮሚያ ክልል በርካታ የሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደቆየ ጠቁመው ስምምነቱ ድርጅታቸው ማዕከሉን አዲስ አበባ አድርጎ የሰብዓዊ ድጋፎቹን በተቀላጠፈ መልኩ በሚንቀሳቀስባቸው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለማዳረስ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርላቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ካሪታስ ሲዊዘርላንድ (CARITAS Switzerland) በስዊዘርላንድ ሀገር ከተመሰረተ 45 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በኢትዮጵያ በአዲሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሰ ያለና በአሁኑ ወቅትም ከ10 በላይ በሚሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ በአፍሪካ፣ በኢስያ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በአውሮፓ እንዲሁም አሜሪካ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ የስምምነት ሰነድ የምስራቅ አፍሪካ ሪጅናል ቢሮውን በአዲስ አበባ ለመክፈት የሚያስችለው ነው፡፡