ድርጅትዎን ከማስመዝገብዎት በፊት ፣ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ሰነዶች ከምዝገባ ፎርም (ዎች) ጋር ተሟልተው መቅረባቸውን ማረጋገጥ ይኖርብዎታል።

ለምዝገባ የሚያስፈልጉ ሰነዶች

ለመመዝገብ የሚፈልጉ የሃገር በቀል ድርጅቶች ማመልከቻቸውን በፊርማ በማስደገፍ የሚከተሉትን ዝርዝሮች ማቅረብ ይኖርባቸዋል:-

  • የመሥራቾችን ሥም፣ አድራሻና ዜግነት የያዘ የምሥረታ ቃለ-ጉባኤ፤
  • የመሥራቾች የመታወቂያ ወይም የፓስፖርት ኮፒ፤
  • የድርጅቱን ሥም እንዲሁም ዓርማ (ካለው)፤
  • የድርጅቱን ዓላማ እና ሊሰማራ ያሰበበትን የሥራ ዘርፍ፤
  • ሊሰማራ ያሰበበትን የሥራ ቦታ (ክልል)፣
  • በመሥራቾች የፀደቀ መተዳደሪያ ደንብ፣
  • የድርጅቱን አድራሻ።

የውጭ ድርጅት ከላይ ከተጠቀሱት ሁኔታዎች በተጨማሪ ከሚከተሉት ሰነዶች ጋር አብሮ ይመጣል:-

  • ድርጅቱ መቋቋሙን የሚያሳይ ከተቋቋመበት አገር የተሰጠው በአግባቡ የተረጋገጠ ሰነድ፣
  • ሥልጣን ያለው የድርጅቱ አካል ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰራ ያሳለፈው በአግባቡ የተረጋገጠ ውሳኔ፤
  • በአገር ውስጥ ተወካዩ የተሠጠው በአግባቡ የተረጋገጠ የውክልና ሥልጣን፣ከተቋቋመበት ሀገር ኤምባሲ ወይም ኤምባሲ ከሌለ ከተቋቋመበት ሀገር ስልጣን ባለው አካል የተሰጠ የድጋፍ ደብዳቤ ወይም ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ የድጋፍ ደብዳቤ፤
  • ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ የሚተገበር የሥራ ዕቅድ።

የኅብረቶች የምዝገባ ማመልከቻ በተወካያቸው ድርጅት ኃላፊ አማካኝነት ተፈርሞ ከሚከተሉት ሰነዶች ጋር ተያይዞ ይቀርባል:-

  • በኅብረቱ መሥራች ድርጅቶች ተወካዮች የተፈረመ የመተዳደሪያ ደንብ፣
  • አባላት ኅብረቱን ለመመስረት የተስማሙበት ቃለ ጉባዔ፣
  • ለኅብረቱ አባላት ከኤጀንሲው ወይም ሥልጣን ካለው የክልል አካል የተሰጠ የአባላት የምዝገባ የምስክር ወረቀት፣

አመልካቹ አግባብነት ባለው ደንብ የሚወስነውን የምዝገባ ክፍያ ይከፍላል።

የሙያ ማኅበራትን ምዝገባ እና አስተዳደር ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቦርድ መመሪያ ሊያወጣ ይችላል።

ሊወርዱ የሚችሉ ቅጾች

ለአዲስ ሀገር በቀል ድርጅቶች የምዝገባ ማመልከቻ ቅጽ
አዲስ የኅብረቶች የምዝገባ ማመልከቻ ቅጽ
አዲስ የውጭ ድርጅት የምዝገባ ማመልከቻ ቅጽ