በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከኢንተር ሚኒስትሪያል ታስክ ፎርስ ሴክሬተሪያት (Inter ministerial task force secretariat) ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር ባጠኑት ጥናት የተመላከቱ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ መንግስት እየወሰደ ያለውን ርምጃ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ማብራሪያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት መንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማሳተፍ በርካታ ስራዎች እየሰራ ይገኛል በማለት የሰብዓዊ መብት አያያዝን በማሻሻል ረገድ ሀገራችን ምን ላይ ነች በሚለው ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሀሳብ መስጠትና መስራት የሚጠበቅባቸው በመሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል፡፡

መንግስት በሁሉም ዘርፍ ለመድረስ ውስንነት ይገጥመዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ውስንነት ለመቅረፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከግሉ ሴክተር ጋር በመቀናጀት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የኢንተር ሚኒስትሪያል ታስክ ፎርስ ሴክሬተሪያት (Inter ministerial task force secretariat) ዶ/ር ታደሰ ካሳ በመንግስት በኩል ጥናቱን መሰረት በማድረግ መንግስት እየወሰደ ያለውን ርምጃ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ተወካዮች ያብራሩ ሲሆን የታስክ ፎርሱ አወቃቀርና የስራ እንቅስቃሴ ላይ ገለፃ አድርገዋል፡፡ የውይይት መድረኩን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ካውንስል በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ ያዘጋጀው ነው፡፡


አድዋ

May be an image of text

የአድዋ ድል የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ድል ከመሆኑም በላይ ጊዜ የማይሽረዉ በደምና በአጥንት የተፃፈ የጋራ ታሪካችን ጭምር ነዉ፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከት የአድዋ ድል ትሩፋት ከጦር ሜዳ አሸናፊነት በላይ ነዉ፡፡ አገራዊ እንድነታችንና ሉዓላዊነታችን የተረጋገጠበት ታሪካዊ ድል ነው፤አድዋ፡፡ የአሸናፊነታችን ምሥጢር መተባበራችንና አንድነታችን ስለመሆኑ አባቶቻችን በተግባር ያስተማሩበት የተግባር ልምምድም ነበር፡፡ መላዉ ኢትዮጵያዊያን ያለ አንዳች ልዩነት በአንድነት ለአገራቸዉ ሉዓላዊነትና ለሕዝቦቿ ክብር ተሰልፈዉ በጋራ የተዋደቁና የጋራ ድል ያስመዘበገቡ በመሆናቸዉ የአድዋ ድል የጋራ ታሪካችን ነዉ፡፡ ከሁሉም በላይ አድዋ የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭም ነዉ፡፡ ከኢትዮጵያም አልፎ የመላ ጥቁር ሕዝቦች ኩራት ነዉ፡፡ የአድዋ ድል የአፍሪካዊያን የነፃነት ፋና ወጊ በመሆን የነፃነት ትግል ማቀጣጠያ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም ተምሳሌት ተደርጋ አንድትቆጠር አድርጓታል፡፡

(ከየመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከተሰጠ መግለጫ የተወሰደ)

የዘንድሮ 126ኛው የአድዋ በዓል “አድዋን ለኢትዮጵያውያን ኅብረት፣ ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የጥቁር ህዝቦች ኩራት ለሆነው ለ126ኛ የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡


ከ350 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ማድረስ መቻሉ ተገለጸ፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የ2014 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸሙን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየገመገመ ይገኛል፡፡
በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፍትህ ሚንስቴር ሚኒስትር ደኤታ አለምአንተ አግደው እንደገለጹት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሃገራችን የልማት እንቅስቃሴ እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳላቸው በመንግስት በኩል ጽኑ እምነት አለ ያሉ ሲሆን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በታሪክ የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በሃገራዊ ጉዳዬች ላይ በተለይም የህግ የበላይነት በማረጋገጥ፣ሰላምን በማስፈንና ግጭቶችን በመፍታት ሂደት ትርጉም ባለው መልኩ አዎንታዊ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከግዜ ወደ ግዜ የተሻለ አቅም እየገነቡ እና መልካም አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሃገራዊ ጉዳይ ሲማዶች በጦርነትና በድርቅ ለተጎዱ አከባቢዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች በገንዘብና በዓይነት እያደረጉ ያሉት ድጋፍ አንድ ለህዝብ ተጠቃሚነት ከቆመ ዘርፍ የሚጠበቅ በመሆኑ ምስጋና የሚገባው መሆኑን በመጠቆም ሲማዶች በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይም ሆነ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ እያደረጓቸው ያሉት አስተዋጽኦዎች መንግስት ከፈጠረው ምቹ ሁኔታ እና ከሃገርና ህዝብ ፍላጎት አንጻር አሁንም ብዙ የሚቀረው ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዘርፉ ህግና ስርዓትን ተከትሎ ውጤታማ ስራ እንዲያከናውን የጀመረውን የክትትል፣የድጋፍ፣የአሳታፊነት እና ቅንጅታዊ ስራ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲሉ የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ላስመዘገቡት መልካም ውጤት አመስግነዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው በሀገሪቱ ላይ የመጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ከጸጥታ ኃይላችን ጎን ለጎን በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ሂደት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አይተኬ ሚና የተጫወቱ መሆኑን አንስተው ባለስልጣን መስሪያቤቱ ያቀረበላቸውን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው ከ350 ሚሊየን ብር በላይ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከጊዜ ወደጊዜ የአሰራር ስዓቱን በማዘመን ከ45 በላይ አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ ሰርቪስ በመስጠት ላይ ይገኛል ሲሉ በመግለጽ የተቋሙን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለማጎልበት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ የምክክር መድረኮችን በማድረግ ወጥነት ያለው የአሰራር ስርዓት ለማጎልበት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሌላው ዋና ዳይሬክተሩ ያሱት ለዘመናት ስንናፍቀው የነበረው ታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን ሆኖ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት በጀመረበት ማግስት መሆኑና የዚህ ድል ባለቤት በመሆናችን እኳን ድስ ያለን ብለዋ፡፡ ከሪፖርቱ በተጨማሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከባለስልጣን መስሪያቤቱ ጋር በቀጣይ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዛሬው እለት የኢ-ሰርቪስ አገልግሎትን በይፋ ያስጀምራል፡፡


በ2014 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች በተገኙበት ውይይት ተደረገ፡፡

የሲቪል መማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ በተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በእለቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እና ምክትል ዋና ዳይሬከተር አቶ ፋሲካው ሞላ ተገኝተዋል፡፡ ውይይቱን በንግግር ያስጀመሩት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በ2013 በጀት አመት የታዩ ክፍተቶችን በመለየት የማስተካከል ስራ ለመስራት፤ የውስጥ አሰራራችንን የመፈተሽና የማዘመን ስራን ትኩረት በማድረግ፤ አመራሩና ሰራተኛው በአመለካከት፣ በእውቀትና በክህሎት ሊያድግ በሚችልበት የሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሁም የሲቪል ማሀበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ህግን የተከተለና የሀገራችንን ክብርና ብሄራዊ ጥቅማችንን ያከበረ መሆኑን በጠንካራ የክትትልና ግምገማ ስርዓት ለማረጋገጥ አቅደን ስንቀሳቀስ ቆይተናል ብለዋል፡፡ የተቋሙ ሰራተኞች የኪራይ ሰብሳቢነትንና ብልሹ አሰራርን አምርረው የሚታገሉበት፤ የጋራ እሴቶቻችንን በጋራ የምናሰርጽበትና መልካም አስተዳደርን የምንገነባበትን አሰራር በተጠናከረ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ በማቀድ የጀመርንት አመት ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ዓመቱን ስንጀምር እንደስጋት ከለየናቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ሀገር ሰላምና አለመረጋጋት እንዲሁም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በእንቅስቃሴያችን ላይ

ሊያስከትሉ የሚችሉ ችግሮችን፤ በተለይም በመስክ ክትትል ስራዎችና ለጥናትና ምርምር ስራዎች የሚሆኑ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ ልንቸገር እንደምንችል አስበን የነበረ ቢሆንም እንደ አሸባሪው የህውኃት ቡድን ግን ጉዳት ያደረሰብን የለም፡፡ ሌሎች በርካታ እንደስጋት የተያዙ ችግሮች ቢኖሩም የመጀመሪያውን መንፈቅ አመት ከእቅድ አንጻር አጠናቀናል ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ግንባታ ስራ ፣የሰው ሃይል ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሃገርን ጥቅም በመጠበቅ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የክትትልና ቁጥጥር ስራ መስራት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን የማስፈን ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ አቅደን ካከናወናቸው አንጻር ያስመዘገብናቸው ስኬቶችም ሆኑ ውስንነቶች ውስጥ የእያንዳዳችን አስተዋጽኦ ያለበት መሆኑን በመረዳት ጠንካራ አፈጻጸሞችን አጠናክሮ መቀጠል እንዲሁም ውስንነቶችንም በማረም በእውቀትና በክህሎት የበቃ፣ ለመማርና ለመለወጥ ዝግጁ የሆነ፣ ቅንና ሁሌም ለውጤት የሚተጋ ከሙስናና ከብልሹ አሰራር የጸዳ የህዝብ አገልጋይ ሰራተኛ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸው እኛ ተግተን ስንሰራ ነው ሌሎች ሊያግዙን የሚችሉት፤ ስለሆነም ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሀገራችን ተግተን ልንሰራ የሚገባው ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ለሰራተኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት የምንመራው ተቋም በሃገሪቱ የማይተካ ሚና ያለው፤ የተቋሙ ስኬት ስኬታችን ውድቀቱ ደግሞ ውድቀታችን በመሆኑ ሁላችንም የምንወረውረው ጠጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እዳለው መረዳት ይኖርብናል ካሉ በኋላ ከዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በትጋት፣ በታታሪነት፣ ስነምግባርን የተላበሰ ባለሙያ በመሆን ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን ሲሉ ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡: የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ በብዙ ክልከላዎች ያሳለፈ ዘርፍ በመሆኑና በአግባቡ መደገፍና መምራት ባለመቻላችን ሀገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያክል ጥቅም አላገኘችም የሚል ቁጭት ያለ በመሆኑ ካለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ወዲህ ግን ዘርፉን ደግፎና አብቅቶ የህዝባችንን ችግር ሲፈቱ ማየት ነው የምንሻው ስለሆነም የመጨሻው መሰረታዊው መለኪያችን እኛ ባደረግነው ክትትልና ድጋፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች  የኅብረተሰቡን ችግር ፈትተዋል ወይስ አልፈቱም የሚለው ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ድርጅቶችን ከመዝጋት ይልቅ በቅጣትና ድጋፍ በማድረግ መስራት የሚችሉትን ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተገቢ ነው ብለው በወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ሳይጸድቅ ቢቆይም ደንቡ ጸድቆ ወደስራ ሲገባ ግን ዳግም ያልተመዘገቡ ድርጅቶች በቅጣት ዳግም ምዝገባ አድርገው ወደ ስራ የሚገቡበት አግባብ ይኖራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከሶስት መቶ ሚሊየን ብር በላይ ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ በአፋር፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር በጦርነትና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አድርገናል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ሀገራችን ችግር ላይ በወደቀችበት ጊዜ አለን ያሉ ድርጅቶችን እውቅና መስጠትና ማበረታታት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ራሱን እንደገና ሪፎርም ወደማድረግ ሂደት መግባት አለበት ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እያንዳንዱ የስራ ክፍል ራሱን በማየት ማስተካከልና  በአዲስ መንፈስና የለውጥ አስተሳሰብ ሀገራችንን ከመቼውም ጊዜ በተለየ ለማገልገል ያገኘነው እድል መሆኑን በመረዳት ወደስራ ልንገባና ውጤታማ አፈጻጸም ልናሳይና ስም ያለው ተቋም ልንገነባ ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በእለቱ የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በእቅድ በጀትና ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ቃልኪዳን መንግስቴ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ከከፍተኛ አመራሮችና ከየስራ ክፍሎቹ ሀላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡


ማንኛውም ሰው ፈቃድ ሳይወስድ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ በማቋቋም ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እንዳይሰራ ተከለከለ::

ማንኛውም ሰው ፈቃድ ሳይወስድ የበጎ አድራጎት ኮሚቴ በማቋቋም ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እንዳይሰራ መከልከሉን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስታወቀ። ከዚህ ቀደም ፈቃድ ሳይኖራቸው የበጎ አድራጎት ኮሚቴ አቋቁመው በገንዘብ ማሰባሰብ ላይ የሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች ከባለስልጣኑ ፈቃድ በመውሰድ ወደ ህጋዊ አሰራር መግባት እንዳለባቸውም አሳስቧል። ይህንን ተግባራዊ በማያደርጉ አካላት ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ አስፈላጊውን ርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። ከባለስልጣኑ ፈቃድ ሳይኖራቸው በህዝብ ስም በማንኛውም መንገድ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራዎችን መስራት የተከለከለ መሆኑን የገለጸው የባለስልጣኑ መረጃ፤ በህዝብ ስም የሚሰበሰብ ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ እንዳይባክን የመከላከልና የመጠበቅ ስልጣን እንዳለው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።
May be an image of text

ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አመራርና ባለሙያዎች በትራንስፎርሜሽን ሊደርሺፕ፣በአገልግሎት አሰጣጥና በፋይናንስ አመራር ላይ ስልጠና አየተሰጠ ይገኛል ፡፡

ተቋሙ ከጀስቲስ ፎር ኦል ጋር በመተባበር በሁለት ዙር ያዘጋጀው ስልጠና ሲሆን በኢፕሳስ (IPSAS) ግንዛቤ እና አተገባበር ዙሪያ ትኩረት እንደሚያደር ተገልጿል፡: በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት ቀደም ሲል ተቋማችን በርካታ የሪፎርም ስራዎችን እየሰራ እንደነበር በማስታወስ በተለይም የባለሙያውን አቅምና ክህሎት ማሳደግ ትኩረት ከተሰጡት ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለተቋሙ የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣትና ውጤታማ ስራ ለማከናወን ጥረት እያደረገ መሆኑን በመናገር ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት አቅም ግንባታ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለውጡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተሻለ ለውጥ በተቋሙ እየተመዘገበ ነው ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ የተሻለ የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ያላቸው ባለሞያዎችንም እያፈራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ አያይዘውም በቀጣይ ተጨማሪ ሙሉ አቅም ያላቸው በርካታ ባለሙያዎችን ማፍራት ይጠበቅብናል ለዚህም ሲባል ነው ቴክኖሎጂን ያማከሉ አለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረጉ ስልጠናዎችን እንድትወሰዱ የተደረገው ሲሉ ለሰልጣኞች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የጀስቲስ ፎር ኦል መስራችና ዳይሬክተር እንዲሁም የኢትዮጵያ የሃገር ሽማግሌዎች መማክርት አባል የሆኑት ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ በሰላም ዙርያ ያዘጋጁትን ዶክመንተሪ ፊልም ማብራርያ እየሰጡ በሃገር ሰላም ዙርያ ልምዳቸውን ለሰልጣኞች አካፍለዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በዋናነት ከተሰጡት ተግባርና ሃላፊነቶች መካከል ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ሲሆን ይህም በፋይናንስ አመራር ላይ የተዘጋጀው ሰልጠና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያቀርቡትን ሪፖርቶችን በአግባቡ መገምገም እንዲቻል እንዲሁም ተገቢውን ግብረመልስ ለመስጠት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ከመረጃዎችም ለመረዳት እንደቻልነው ይህ የኢፕሳስ(IPSAS) አሰራር130 በላይ ሃገራት እንደሚጠቀሙበት ተመላክቷል፡፡


ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፖዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር በማህፀን በር ካንሰር ላይ ለተቋሙ ሴት ሰራተኞች ስልጠና ሰጠ፡፡

የተቋሙ የሴቶች ፎረም የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያና አዲስ የፎረም አባላትን የመመዝገብ ስነስርዓትም ተካሂዷል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ባዘጋጀው በዚህ የስልጠና መርሃ ግብር ላይ የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦን ጨምሮ የፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ሲኒየር ዳይሬክተር ዶ/ር ንጉሱ ተገኝተዋል፡፡ ስልጠናው በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው በማህፀን በር እና በጡት ካንሰር ላይ ሲሆን ዓቢይ ዓላማውም የተቋሙ ሴት ሰራተኞች ስለማህፀን በር ካንሰር አስከፊነት ግንዛቤ ወስደው ቅድመ የማህፀን በር ምርመራ በማድረግ ከዚህ አስከፊ በሽታ ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡

የባለሥልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በስልጠናው ማስጀመሪያ ወቅት እንደተናገሩት ጤና በእጃችን ሳለ ብዙ ትኩረት የማይሰጠው፤ ስናጣው ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ገልፀው ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን የጤናችንን ጉዳይ ልንከታተል ይገባል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ሁላችሁም እንደምታውቁት ቀደም ባለው አዋጅ የተነሳ ድርጅቶች ወደኛ ለመቅረብ ይቸገሩ እንደነበር አንስተው አዲሱ አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ከወጣ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ግን የህግ መሻሻል ብቻ ሳይሆን ድርጅቶችና አጋር አካላት ለተቋማችን ያላቸው አመለካከት እየተሻሻለና እየተቀየረ መጥቷል፤ በዚህም የተነሳ ነው ከድርጅቶች ጋር በመተባበር መሠል ስልጠናዎች እየተዘጋጁ ያሉት ብለዋል፡፡ ለአንድ ተቋም ስኬት የሰው ኃይል ትልቅ ትልቅ ሚና አለው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ክህሎት ያለው፣ በዕዉቀት የዳበረ፣ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ ቅንነት ያለው ሰራተኛ ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ ተቋሙም ሞዴል ተቋም እንዲሆንና ቀልጣፋና አርኪ ስራዎችን ለመስራት የተቋማችን ሰራተኞች ጤናማ፣ ስነ ምግባርን የተላበሱ ታታሪ ሰራተኞች እንዲኖሩን ይገባል፤ በተቋማችን ያሉ ሴት አመራሮችም እጅግ ስኬታማና ስራቸውን የሚያከብሩ በመሆናቸው ባለሥልጣን መስሪያ ቤታችን ያመሠግናቸዋል ሲሉ አክለው ገልፀዋል፡፡

የፖዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ሲኒየር ዳይሬክተር ዶ/ር ንጉሱ በበኩላቸው ፓዝ ፋይንደር እ.ኤ.አ ከ1966 ጀምሮ ፓስ ፋይንደር ፈንድ በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ መሠረቱን የጣለ ድርጅት መሆኑን አንስተው ለረጅም አመታት በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል፡፡ የማህጸን በር ካንሰር በዓለም ላይ አደገኛ ከሆኑ በሽታዎች በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደሆነ ጠቁመው ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ ከ15-20 አመት ሊቆይ ይችላል ብለዋል፡፡ አክለውም በሽታውን ስር ሳይሰድ መከላከል እንደሚቻልና ማንኛዋም ሴት በየ5 አመት ልዩነት በመመርመርና ህክምና በመውሰድ በሽታውን መከላከል እንደምትችል አንስተው ድርጅታቸው ከ2019ዓ.ም ጀምሮ ሲንግል ቪዚት አፕሮችን በመከተል ሴቶች አፋጣኝ ህክምና እንዲያገኙ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ እንደቆዩ ያነሱት ዳይሬክተሩ መሠል ስራዎችን ወደፊትም አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ የሴቶች ፎረም ውስጠ ደንብ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ተቋሙን ለተቀላቀሉ አዲስ የሴት ሰራተኞች ፎረሙን የማስተዋወቅ ስራ ተከናውናል፡፡ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ጸሀይ ሽፈራው ፎረሙን ባስተዋወቁበት ወቅት ተቋሙ ለሴት ሰራተኞች ልዩ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝና ከ30% በላይ የሚሆኑት ሴት አመራሮች እንደሆኑ አንስተው የተቋማችን ሴት ሰራተኞች እጅግ ምስጉንና ውጤታማ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ይህ የሴቶች ፎረም ሴቶች ልዩ ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ፤ በርካታ ሴቶችም ወደ አመራርነት እንዲመጡ ለማድረግ ከፍተኛ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ሴቶች ማንኛውም በስራ ላይ የሚገጥማቸው ችግር ካለ በማስረጃ ቢያቀርቡልን አፋጣኝ መልስ እንዲያገኙ ፎረሙ ከፍተኛ ስራ የሚሰራ ይሆናል ሲሉም አክለው ገልፀዋል፡፡ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ለፓስ ፋይንደር ኢንተርናሽናል የምስጋና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ለተቋሙም ሴት ሰራተኞች የእንኳን ደህና መጣችሁ ስጦታ በፎረሙ በኩል ተበርክቶላቸዋል፡፡


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃድ የአመራር ማንዋል ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ 1113/2011 በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት የበጎ ፈቃደኝነት ባህልና እንቅስቃሴ ማበረታታት፣ የበጎ ፈቃደኝነት በተመለከተ የስርፀት ስራ መስራት ነው፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሰጠውን ሀላፊነት ለመወጣትና የበጎ አድራጊነት እና የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን በህብረተሰብ ውስጥ ባህል ለማድረግ የበጎ ፈቃድ ስርፀት አመራር ማንዋል ላይ በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጅግጅጋ ከተማ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት አመራሮች ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደተናገሩት አገራችን በለውጥ ጎዳና ውስጥ ከገባች አንስቶ በዋናነት ለውጥ የተደረገው በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡: አያይዘውም ዘርፉ በቀድሞ ህግ የዜጎች የመደራጀት መብት የተገደበበት፣ በሰብዓዊ መብትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ መሰራት የተከለከለበት፣ እንዲሁም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የነበረው አተያይ የተዛባ እንደነበር በመግለጽ አገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ መቅረቷን አንስተዋል፡፡

በለውጡም ማግስት በመንግስት የተወሰደው እርምጃ አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን አዋጅ ሙሉ በሙሉ በመለወጥ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ከፖለቲካ ወገኝነት ነጻ የሆኑ በአገሪቱ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ እና አስተዋጾ እንዲያደርጉ እንዲሁም በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን የመደራጀት መብት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ም/ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ህብረተሰባችን የተጎዳ በመሆኑ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት ስራ የተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚሰራ ሳይሆን በዘላቂነት አጠናክሮ መስራት አስፈላጊ መሆን እንዳለበት በመግለጽ በጎ የሚያደርግ ሰው ክፋት የለውም ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡
በጎ ፈቃደኝነት ስራን ተቋማዊ ለማድረግ በህግ መደገፍ አለበት፤ፖሊሲም እየወጣ ነው፤ ባለስልጣኑም ማንዋል በማዘጋጀት በየክልሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡ በስልጠናው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሶማሌ ክልላዊ መንግስት የፋይናንስ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙህዲን አብዲ እንዳሉት ይህን ስልጠና በክልላችን ለመስጠት በመምጣታችሁ ደስተኛ ነን በማለት የባለስልጣን መስሪያቤቱ ድርጅቶችን ከመመዝገብ ባሻገር የሚሰሩ ስራዎችን በመቆጣጠርና መከታተል እንዲሁም እውቅና መስጠት አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በጎ አድራጊነት ድንበር የለውም ያሉት ቢሮ ሀላፊው በዋናነት መንግስትም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ህዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል፡፡