ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባዘጋጀው የክትትልና ግምገማ ማንዋል ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረቶች በተገኙበት የማስተዋወቂያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡ በማስተዋወቂያ መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት እንዳሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር ብልጽግናና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ድጋፋዊ የሆነ የክትትልና የግምገማ ስርዓትን በመዘርጋት ቀልጣፋና ተገማች የሆነ አሰራርን ለመዘርጋት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዘርፉ ላይ የመንግስት አማካሪ እንደመሆኑ መጠን በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ ያስፈልገዋል፡፡ ስለሆነም የክትትልና የግምገማ ስርዓታችንን ማስተካከልና ማዘመን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ አክለውም በዚህ የክትትልና የግምገማ ማንዋል መሰረት ለድርጅቶች ደረጃ የሚሰጥ ሲሆን ዘርፉ በሀገሪቱ GDP ላይ ያለው አበርክቶ ለመለየት ትልቅ ሚና ስለሚኖረው በዘፈቀደ ከሚወሰኑ ውሳኔዎችም የሚታደግ ነው ብለዋል፡፡