በመድረኩ ላይ በርካታ የክልል እና የፌዴራል የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት እና የኢትዬጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የኢፌዴሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዬን ጢሞቲዬስ ባስተላለፉት መልዕክት በባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት ልዩ አጽንኦት በመስጠት ህጉን ማሻሻል መቻሉን ገልጸው በአንድ ሃገር የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተዋናዬች በተጨማሪ ያለትርፍ ለበጎ አድራጎት ተግባር ተሰባስበው እና ተደራጅተው የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ሃገራዊ ሁኔታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ሲገልጹ በሃገሪቱ በግጭት ምክንያት የወደሙ መሰረተ ልማቶችና ንብረቶችን ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ መልሶ የመገንባት፣ቁሳዊ ያልሆነውን የወንድማማችነትና አብሮነት በተመለከተ እርቅ ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንዲሁም እንደዚህ ዓይነት የግጭት ምንጭ የሆኑ ጉዳዬችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠት የተቋቋመውን የሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሚጠራው የውይይት መድረኮች ላይ ተሳታፊ መሆን እና የማገዝ ስራ መስራት እንደሚገባ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት የምክክር መድረኩ ዓላማ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የተከናወኑ ዐበይት ሥራዎችን በመገምገም፣ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ማረም፤ ማጽናትና ማላቅ በሚገቡን ጉዳዮችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ጉባኤው ተወያይቶ ማስቀመጥ ብሎም በዘርፉ ሚታዩ ክፍተቶችንም በመለየት የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥና ምርጥ ተሞክሮዎችን መለዋወጥም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተፈጠረው ችግር በርካታ ችግሮች የደረሱ መሆኑን ገልጸው ይህንን ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውንና በከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙትን ወገኖቻችን መደገፍ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ቢሆንም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከዚህ አንጻር ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰብዓዊ ዕርዳታና ድጋፍ በማሰባሰብ “እኔም ለወገኔ” በሚል ከቀዬቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ድጋፍ የሚውል ሀብት በማሰባሰብና በቦታው በማድረስ ጭምር ያደረጉት ርብርብና አሁንም በማድረግ ላይ የሚገኙት ድርጅቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከመንግስት ጎን በመቆም ሀገርን ከአደጋ ለመታደግ ያሳዩት ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ለሲዳማ ብ/ክ/መንግስት እዲሁም ወጪውን በመሸፈን ተባባሪ ለሆነው CSSP2 ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡