የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሴቶች ማኅበር ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር አዲስ ለተቀጠሩ ሰራተኞች በአካል ጉዳተኛ ሴቶች አካታችነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡ በስልጠናው ላይ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማኅበር ስራ አሲኪያጅ ወ/ሮ ድባቤ ባጫ እንዳሉት ማኅበሩ ከተመሰረተ ሃያ ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን በአሁን ሰዓት በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም በዋናነት ማኅበሩ የሚሰራቸው ስራዎች የአቅም ግንባታ ስጠናዎች፣ የገቢ ማስገኛ ስራዎች፣በመብትና ጥቅሞች ላይ እየሰራ እንደሆነ በመግለፅ ይህ ስልጠና ያስፈለገው በአካል ጉዳተኛ ሴቶች አካታችነት ላይ ለባለስልጣኑ ሰራተኞች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት አዲሱ አዋጅ 1113/2011 ለአካል ጉዳተኞች ሰፊ እድል የሰጣቸው ሲሆን በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቦርድ ውስጥ ያላቸው ውክልና ከፍ ያለ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አክለውም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማንኛውንም ስራ ሲሰሩ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካቶ መስራት እንዳለባቸው በማንሳት እንዲሁም መመሪያዎችም ሆኑ ህጎች ሲዘጋጁ አካል ጉዳተኞችን ባካተተ መልኩ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ሌላው ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለአካል ጉዳተኞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ ሲሆን ለአገር ልማትና እድገት ለማምጣት ለሚሰሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል፡፡