ልጆች ላይ የዘሩት ለትውልድ ይተርፋል!!





ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ድርጅቱ ብዙ ለሃር የሚጠቅም ፕሮጀክትን ይዞ እየሰራ የሚገኝ መሆኑን በመግለጽ ሃገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በጎ ማድረግ አስፈላጊ ነው ፡፡ በጎ ስራ የሰሩ እና እየሰሩ ያሉ ሰዎች እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ በመሆናቸው ስራቸው ለአዲሱ ትውልድ ሊነገር ይገባል ይህንን ደግሞ ለማድረግ መንግስትም ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡



የከበረ ዝግባ ቀንበጥ የበጎ አድራጎትና የልማት ድርጅት የስራ እንቅስቃሴ በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ተጎበኘ፡፡
የከበረ ዝግባ ቀንበጥ የበጎ አድራጎትና የልማት ድርጅት ከአዲስ አበባ 70 ኪሎሜትር ላይ በምትገኘው ውጫሌ ወረዳ ይገኛል፡፡ የመስክ ምልከታውን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ የሆፕ ቸስት ቺልድረንስ (children’s hope chest) የስራ ሃላፊዎችና ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ከመጡ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ድርጅቱን ጎብኝተዋል ፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ስለድርጅት አመሰራረት ገለፃ ያደረጉልን የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሪት ስምረት መንገሻ እንዳሉት ድርጅቱ ሲቋቋም ዓላማ አድርጎ የተነሳው ወላጅ አልባ የሆኑትና ለጥቃት የተጋለጡ ህፃናት የትምህርት፣ የምግብ፣ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ቤተሰባቸውን፣ ህብረተሰባቸውን እንዲሁም ሀገራቸውን የሚወዱና በራሳቸው ሚተማመኑ፣ ሃላፊነት የሚሰማቸው፣ ከጥገኝነት ነፃ ሆነው እንዲያድጉ ለማድረግ ተብሎ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል፡፡



ስራ አስኪያጇ አክለውም ድርጅቱ በአሁን ጊዜ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ከ50 በላይ ህፃናትን በስሩ አቅፎ በጤናና በትምህርት ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ በመግለፅ በተጨማሪም ከ120 በላይ የሆኑ ህፃናትን ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው በትምህርትና በጤና አገልግሎት ድጋፍ እያደረጉላቸው እንዳለም ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም የአካባቢውን ህብረተሰብ ከልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በጥምረት በመስራት ቺልድረንስ ሆፕ ቸስት (children’s hope chest) ከተባለው የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት በተገኘ ፈንድ የንፁህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ በማስቆፈር ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ያስረዳሉ፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ራሱን ለመቻል በገቢማስገኛ ስራ ላይ ከቺልድረንስ ሆፕ ቸስት (children’s hope chest) በተገኘ ድጋፍ በሰፊው በመሳተፍ ላይ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ ስምረት በንብ ማነብ፣የወተት ላሞችን በማርባት ፣በጎችን በማርባት፣የእንቁላል ዶሮችንና የዘይት መጭመቂያ ስራላይ በመሰማራት እንዲሁም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ገቢውን ማሳደግ እንደቻሉና በቀጣይም ይህንኑ በማጠናከር በርካታ ስራዎችን ለመስራት ድርጅቱ ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል ፡፡

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት በተቋሙ እየተሰሩ ያሉት ስራዎችን በማድነቅ እየሰራችሁ ያለው ስራ በተለይም ድርጅቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ከጠባቂነት መንፈስ ለመውጣት በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ እየሰራችሁ ያለው ተግባራት የሚደነቅና የሚበረታታ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ለጋሽ ድርጅቶችም ቢሆኑ እንዴት አድርገን ከችግር ውስጥ መውጣት እንደምንችል መንገድ እንዲያሳዩን እንጂ እስከ ህይወት ዘመናችን እንዲረዱን መፍቀድ አይኖርብንም ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ ራሱን ለመቻልና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ እየሰራ ያለው ስራ ትልቅ ማሳያ መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ለድርጅቱ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም የአገራችን እድገት የሚረጋገጠው መንግስት፣ የግሉ ሴክተር እና የሲቪል ማህበረሰቡ ትስስር ሲፈጥር ነው፡፡ ይህንን ካደርግንና ሁላችንም የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ከተወጣን የህብረተሰባችንን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የማንችልበት እንዲሁም ከልመናም የማንላቀቅበት ምክንያት አይኖርም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡



የሲቪል ማህበረሰብ ድጅቶች ኤጀንሲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አውት ኦፍ ዘ አሽ (out of the ash) የተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የስራ እንቅስቃሴን ጎበኙ፡፡
ድርጅቱ ‹‹የድህነትን ዑደት በትምህርት እንስበር›› የሚል መሪ ቃል አንግቦ በተለምዶ ቆሼ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ ህጻናትንና ወጣቶችን የትምህርት፣ የጤና፣ የምግብና የአልባሳት፣ የመጠለያ እንዲሁም ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እየደገፈ የሚገኝ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ ከተመለከቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ ትምህርትን አንዱ የድህነት መቀነሻ መሳሪያ አድርጎ መጠቀሙ ባለትልቅ ራዕይ መሆኑን የሚያመላክት ነውና ለወደፊቱም አጠናክራችሁ መቀጠል ይኖርባችኋል ሲሉ ለድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡





በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር የሆኑትን ክቡር ሬሚ ማሬሾ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በቢሮአቸው አግኝተው አነጋግረዋቸዋል፡፡
በውይይቱ በሃገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ የመጡ ለውጦች፣አዲሱ አዋጅ ከተለወጠ በኋላ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመንግስት ጋር አብሮ ከመስራት አንጻር ያላቸው ሚና ፣ ከAFD የተባለ ፈረንሳይን መሰረት ያደረገ ድርጅት ከኤጀንሲው ጋር የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድን ከማገዝ አንጻር የተጀመሩ ስራዎች በተመለከተ እንዲሁም በቀጣይም የኤጀንሲውን አቅም ከመገንባት እና የልምድ ልውውጥ ከማድረግ አንጻር አብሮ ስለመስራት ተወያይተዋል፡፡



"በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ!"
“በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል 14ኛው የብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በኤጀንሲው ተከብሯል፡፡
የዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው በንግግራቸው እንደገለጹት የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የሚከበረው አዲስ ፓርላማ እና የመንግስት ምስረታ በተካሄደበት ማግስት እና በኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመገንባትና ብልፅግናን ለማምጣት አዲስ ምእራፍ በጀመርንበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል በማለት እኛም እንደ ዜጋ በአዲስ ራዕይ እና በአዲስ ተስፋ ሃገራችንን ማገልገል አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡



የሲ.ማ.ድ.ኤ. የኮሚዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት
ኤጀንሲው ከ45 በላይ አገልግሎቶችን በኦን ላይን ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገለፀ ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የአሰራር ዘይቤውን በመቀየር ቀደም ሲል በወረቀት ይሰጥ የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ከአርባ አምስት በላይ በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በኢ-ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀ፡፡
በተቋሙ ውስጥ አገልግሎቱን ለመጀመር ለተቋሙ ባለሙያዎችና ሃላፊዎች በአገልግሎት አሰጣጡና በአጠቃቀሙ ዙርያ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የተቋሙን ባለሙያዎች ሲያዘጋጅ እንደቆየ ይታወሳል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስለ አገልግሎቱ አጠቃቀምና በአገልግሎቱ ስለተካተቱ የተቋሙ አገልግሎቶች በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ገለጻ አድርገጓል፡፡

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት ላለፉት ሶስት ዓመታት በሃገራችን በነበረው የለውጥ ሂደት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሁለተናዊ ብልፅግና ላይ የራሳቸውን ሚና መጫወት እንዲችሉ ህግና ተቋማዊ ሪፎርሞች መካሄዳቸውን በማስታወስ በቅርቡም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር የመንግስት አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ እንዲሰጡ ለማድረግ በጀመረው እንቅስቃሴ መሰረት ኤጀንሲያችን የኢ-ሰርቪስ አገልግሎትን በማስጀመር ተቋማችን ወደ ተሻለ የአገለግሎት አሰጣጥ እንዲሸጋገር በማድረግ የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር የአይ ሲቲ ልማት ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ኢንጂነር አብዮት ሲናሞ በበኩላቸው በሃገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ወደፊት እንዲራመድ ለማድረግ ባለፉት አመታት የሃገሪቱ የኢ ትራንዛክሽን አዋጅ ፀድቆ ስራ ላይ መዋሉ ይታወሳል፤ ይህም በዋናነት ቀደም ሲል በወረቀት ይሰሩ የነበሩ አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ ቢሰሩ ህጋዊነታቸውን አያጡም የሚል መሰረታዊ የህግ ማዕቀፍ ማስቀመጡን ገልጸዋል ፡፡ አያይዘውም በዚህ የህግ ማዕቀፍ መሰረት የ E_government ስራዎች ማለትም መንግስት ከዜጎች፣ መንግስት ከንግዱ ማህበረሰብ ወይም የመንግስት ተቋማት ከመንግስት ተቋማት ጋር የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች በሂደት ወደ ኤሌክትሮኒክስ መጠቀሚያ ዘዴ እንዲቀየሩ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል ፡፡



በአገልግሎቱ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ቴክኖሎጂው ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ ያላስፈላጊ እንግልትን የሚያስቀር መሆኑን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ የመንግስት ተቋማት አገልግሎታቸውን ዲጂታል በማድረግ የኢ ሰርቪስ አገልግሎት እንዲሰጡ ከተመረጡ 20 የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አንዱ ሲሆን በተቋሙ የሚሰጡ አርባ አምስት አገልግሎቶች በኢ ሰርቪስ የሚሰጡ ይሆናል፡፡ በአገልግሎቱ ላይ የሚነሱ አስተያየቶች ካሉም ለኤጀንሲው ማሳወቅ የሚቻል መሆኑም ታውቋል፡፡

የኤጀንሲው ስኬት የሚለካው የተመዘገቡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚያስመዘግቡት ውጤት እንደሆነ ተገለፀ፡፡






ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ለኤጀንሰው የአስር ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ ዝግጅት ቴክኒካል ድጋፍ ከሚሰጠው ከFCG-Sweden የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በራስ የውስጥ አቅም የ10 ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ይህ ዕቅድ የተቋሙ ርዕይ ዋነኛ ማዕዘን የሆኑትን ጠንካራ የሲቪል ማህበራት ዘርፍ እንዲፈጠር የማድረግ፤ ብቁና ውጤታማ ኤጀንሲ የመገንባት፣ የህብረተሰቡን የሲቪክ ባህሉ የማዳበር እንዲሁም በአጠቃላይ በሲቪል ማህበራት ዘርፍ እንቅስቃሴ የህብረተሰባችንን የላቀ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራትን የበለጠ ለማሳካት በሚያስችል እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የ10 ዓመት ስትራቴጅክ እቅድ እንዲዘጋጅ ለማድረግ በፈረንሳይ የልማት ትብብር /AFD/ የፋይናንስ ድጋፍ አለም አቀፍ አማካሪ በሆነው በFCG-Sweden እቅዱን የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡



በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ “ነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት” የፊርሚያ ማሰባሰቢያ ይፋዊ የመክፍቻ መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት በሚል የተጀመረውን ሀገር ዓቀፍ ንቅናቄ መቀላቀሉን በግራንድ ኤልያና ሆቴል ባደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ጋዜጣዊ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት የምዕራቡ ዓለም በተለይም አሜሪካ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳያችን ላይ የያዙት አቋምና እያራመዱት ያለው አግባብነት የሌለው ጫናና ጣልቃ ገብነት ስለሆነ ይህንን ጫናና ጣልቃ ገብነት በትክክለኛ መረጃና ማስረጃ ላይ በመመስረት ትክክለኛውን እውነት ተገንዝበው አካሄዳቸውን እንዲመረምሩና እንዲያስተካክሉ ብሎም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ በሲቪል ማህበራት አስተባባሪነት የ “ነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት” ዘመቻ ተጀምሯል ብለዋል፡፡
.በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን የሚጎዳና አንድነታችንን የሚንድ ጉዳይ በመጣ ጊዜ ልዩነታችንን ወደኋላ በመተው በአንድነት ሆነን ለሀገራችን የምንረባረብ ጀግናና ባለታሪክ ህዝቦች መሆናቸንን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የምናሳውቅበትና አንድነታችንንም የምናጠናክርበት ነው ሲሉም አያይዘው ገልጸዋል፡፡


በዛሬው እለት የኤጀንሲው ሰራተኞችና አመራሮች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በይፋ ሀገር አቀፍ ዘመቻውን መቀላቀላቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያበሰሩ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ሰራተኞች በሙሉ ይህን ፈለግ በመከተል በየተቋሞቻቸው የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ዘመቻን ተቀላቅለው በመፈረም ወደ አሜሪካው ቤተ መንግስት የሚልኩ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ካውንስል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን በበኩላቸው ሀገራዊ ሪፎርሙ ከተደረገ ጊዜ ጀምሮ ሀገራችንን ለመቀየር ጥረት እያደረግን እንገኛለን ያሉ ሲሆን ሀገራችን ለጠላት ተጋላጭ እንድትሆን በሚያደርግ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ ሀገራትም ይሁኑ ተቋማት በጽኑ የምናወግዛቸውና መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን ብለዋል፡፡
የመንግስትን አቅም በማዳከም ማህበረሰቡን ለረሀብ ለግጭት ማህበረዊ ቀውስ ለመዳረግ የሚጥሩትን የሚቃወሙ መሆኑን የገለጹት የካውንስሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አሜሪካን ጨምሮ የምዕራቡ ዓለም እያራመደ ያለው አቋም ሀገራችንን ቀውስ ውስጥ የሚከት ስለሆነ ቆም ብለው እንዲያስቡ ለመጠቆም እንወዳለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የዩዝ ኢምፓዎር ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ሰይፉ በበኩላቸው በሀገራችን ላይ እየተደረገ ያለው ጫና በገንዘብ የተገዛን ውሸት ወደ እውነት ለመቀየር እየተደረገ ባለ ሂደት ውስጥ ስለሆነ የሀገራችን ወጣቶች ይህን ተገንዝበው የሀገራችን እውነት አላት፤ ይህን እውነት ደግሞ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያውቀው ይገባል በሚል ይህ ንቅናቄ ሊጀመር ችሏል ብለዋል፡፡



አቶ አለማየሁ አያይዘውም የመንግስት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ ፤የኃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በሀገር ጉዳይ አንድ የሆነ አቋም አለን የሚለውን መነሻ በማድረግ ሀገራችን ሉዓላዊነቷ ከመደፈሩ በፊት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎች ይህን እውነት በደብዳቤው ላይ በመፈረም ወደ አሜሪካው ቤተመንግስት የሚልኩ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የመደራጀት መብት፣ ሰብዓዊነት፣ የኅብረተሰቡ የላቀ ተጠቃሚነት!!!
የሲ.ማ.ድ.ኤ የኮሚኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት
ኤጀንሲው የአፍሪካ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የልህቀት ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል የመግባብያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ኤጀንሲው የአፍሪካ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የልህቀት ማዕከል ለመገንባት ከኢትዮጵያ የሲቪል ማህንዲሶች ማህበር እና ከኢትዬጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት የፊርማ ስነ- ስርዓት አካሂዷል፡፡ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት የዚህ የልዕቀት ማዕከል ሃገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አንስተው በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ስራ በማቀላጠፍና ወደፊት በማራመድ ረገድ ማዕከሉ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍን እንደዋና የልማት አጋርነት መመልከቱን አስታውሰው ዘርፉን ለማጠናከር እና ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዲችል እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቀመር ሀገራችን ከሲቪል ማህበረሰቡ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የልዕቀት ማዕከሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡



በመድረኩ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የኤጀንሲው የስትራቴጂክ አጋርነት ቡድን ከፍተኛ አማካሪ አቶ አንዱዓለም መኮንን እንዳብራሩት የልህቀት ማዕከሉ ሲገነባ የተሻለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለመፍጠር፤ በስልጠናና በትምህርት የዳበረ የሰው ሃይል ለማጎልበት ከዓለማቀፍ ተቋማት በተለይም ከትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እንዲሁም የገቢ ማስገኛ ሆኖ እንደሚያገለግል በገለጻቸው አብራርተዋል፡፡ አቶ አንዷለም አያይዘውም እ.ኤ.አ በ2063 በአፍሪካ የልማት እቅድ ውስጥ ከተያዙ ፒላሮች ውስጥ የአቅም ግንባታ ስራ አንዱ መሆኑን ገልጸው በአፍሪካ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማያያዝና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማምጣት ረገድ ይህ የልዕቀት ማዕከል የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ኤጀንሲው ይህን የልዕቀት ማዕከል ለመገንባት የሚያስችሉ የወረቀት ስራዎች ከግንባታው ጎን ለጎን የሚሰሩ መሆኑን ጠቁመው በ2030 ዓ.ም የያዝነውን የልማት እቅድ ስኬታማ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡



የኢትዮጵያ ኮንሰትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው ተቋማቸው ካሁን በፊት እንደእንጦጦ ፓርክ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በአጭር ግዜ መስራት የቻለ ተቋም መሆኑን አንስተው ይህንንም ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ እንዲሁም ኤጀንሲው ይህን ትልቅ ፋይዳ ያለውን ፕሮጀክት ለማስጀመር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡ የመገባቢያ ስምምነቱን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ኮንሰትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የሲቪል መሀንዲሶች ማህበር ፕሬዝዳንት ተፈራረመዋል፡፡
የመደራጀት መብት፣ ሰብዓዊነት፣ የኅብረተሰቡ የላቀ ተጠቃሚነት!!!
የሲ.ማ.ድ.ኤ የኮሚኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት






