የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት በሚል የተጀመረውን ሀገር ዓቀፍ ንቅናቄ መቀላቀሉን በግራንድ ኤልያና ሆቴል ባደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ጋዜጣዊ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት የምዕራቡ ዓለም በተለይም አሜሪካ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳያችን ላይ የያዙት አቋምና እያራመዱት ያለው አግባብነት የሌለው ጫናና ጣልቃ ገብነት ስለሆነ ይህንን ጫናና ጣልቃ ገብነት በትክክለኛ መረጃና ማስረጃ ላይ በመመስረት ትክክለኛውን እውነት ተገንዝበው አካሄዳቸውን እንዲመረምሩና እንዲያስተካክሉ ብሎም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ በሲቪል ማህበራት አስተባባሪነት የ “ነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት” ዘመቻ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

ይህ ዘመቻ እንዲጀመር በማድረግ፤ እያስተባበሩ የሚገኙት በወጣቶች ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሲሆኑ በዚህ ዘመቻ ላይ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት በቀጥታ መልዕክታቸውን የሚልኩ እንደሆነ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ዘመቻው በኢትዮጵያውያን መካከል አንድነትን የሚፈጥር፤ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያውያንን ትክክለኛ አቋምና እውነታ በመረጃና በማስረጃ እንዲመረምር እንዲሁም መሬት ላይ ያለውን ሀቅ እንዲረዳ ለማድረግ የኢትዮጵያ ወጣቶች በዘመቻው የሚረባረቡ ይሆናል፡:

.በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን የሚጎዳና አንድነታችንን የሚንድ ጉዳይ በመጣ ጊዜ ልዩነታችንን ወደኋላ በመተው በአንድነት ሆነን ለሀገራችን የምንረባረብ ጀግናና ባለታሪክ ህዝቦች መሆናቸንን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የምናሳውቅበትና አንድነታችንንም የምናጠናክርበት ነው ሲሉም አያይዘው ገልጸዋል፡፡

በዛሬው እለት የኤጀንሲው ሰራተኞችና አመራሮች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በይፋ ሀገር አቀፍ ዘመቻውን መቀላቀላቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያበሰሩ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ሰራተኞች በሙሉ ይህን ፈለግ በመከተል በየተቋሞቻቸው የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ዘመቻን ተቀላቅለው በመፈረም ወደ አሜሪካው ቤተ መንግስት የሚልኩ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ካውንስል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን በበኩላቸው ሀገራዊ ሪፎርሙ ከተደረገ ጊዜ ጀምሮ ሀገራችንን ለመቀየር ጥረት እያደረግን እንገኛለን ያሉ ሲሆን ሀገራችን ለጠላት ተጋላጭ እንድትሆን በሚያደርግ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኙ ሀገራትም ይሁኑ ተቋማት በጽኑ የምናወግዛቸውና መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን ብለዋል፡፡

የመንግስትን አቅም በማዳከም ማህበረሰቡን ለረሀብ ለግጭት ማህበረዊ ቀውስ ለመዳረግ የሚጥሩትን የሚቃወሙ መሆኑን የገለጹት የካውንስሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አሜሪካን ጨምሮ የምዕራቡ ዓለም እያራመደ ያለው አቋም ሀገራችንን ቀውስ ውስጥ የሚከት ስለሆነ ቆም ብለው እንዲያስቡ ለመጠቆም እንወዳለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የዩዝ ኢምፓዎር ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ሰይፉ በበኩላቸው በሀገራችን ላይ እየተደረገ ያለው ጫና በገንዘብ የተገዛን ውሸት ወደ እውነት ለመቀየር እየተደረገ ባለ ሂደት ውስጥ ስለሆነ የሀገራችን ወጣቶች ይህን ተገንዝበው የሀገራችን እውነት አላት፤ ይህን እውነት ደግሞ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያውቀው ይገባል በሚል ይህ ንቅናቄ ሊጀመር ችሏል ብለዋል፡፡

አቶ አለማየሁ አያይዘውም የመንግስት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ ፤የኃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በሀገር ጉዳይ አንድ የሆነ አቋም አለን የሚለውን መነሻ በማድረግ ሀገራችን ሉዓላዊነቷ ከመደፈሩ በፊት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎች ይህን እውነት በደብዳቤው ላይ በመፈረም ወደ አሜሪካው ቤተመንግስት የሚልኩ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የመደራጀት መብት፣ ሰብዓዊነት፣ የኅብረተሰቡ የላቀ ተጠቃሚነት!!!

የሲ.ማ.ድ.ኤ የኮሚኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት