ኤጀንሲው የአፍሪካ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የልህቀት ማዕከል ለመገንባት ከኢትዮጵያ የሲቪል ማህንዲሶች ማህበር እና ከኢትዬጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት የፊርማ ስነ- ስርዓት አካሂዷል፡፡ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት የዚህ የልዕቀት ማዕከል ሃገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አንስተው በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ስራ በማቀላጠፍና ወደፊት በማራመድ ረገድ ማዕከሉ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍን እንደዋና የልማት አጋርነት መመልከቱን አስታውሰው ዘርፉን ለማጠናከር እና ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዲችል እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቀመር ሀገራችን ከሲቪል ማህበረሰቡ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የልዕቀት ማዕከሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የኤጀንሲው የስትራቴጂክ አጋርነት ቡድን ከፍተኛ አማካሪ አቶ አንዱዓለም መኮንን እንዳብራሩት የልህቀት ማዕከሉ ሲገነባ የተሻለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለመፍጠር፤ በስልጠናና በትምህርት የዳበረ የሰው ሃይል ለማጎልበት ከዓለማቀፍ ተቋማት በተለይም ከትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እንዲሁም የገቢ ማስገኛ ሆኖ እንደሚያገለግል በገለጻቸው አብራርተዋል፡፡ አቶ አንዷለም አያይዘውም እ.ኤ.አ በ2063  በአፍሪካ የልማት እቅድ ውስጥ ከተያዙ ፒላሮች ውስጥ የአቅም ግንባታ ስራ አንዱ መሆኑን ገልጸው በአፍሪካ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማያያዝና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማምጣት ረገድ ይህ የልዕቀት ማዕከል የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የመሩት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ኤጀንሲው ይህን የልዕቀት ማዕከል ለመገንባት የሚያስችሉ የወረቀት ስራዎች ከግንባታው ጎን ለጎን የሚሰሩ መሆኑን ጠቁመው በ2030 ዓ.ም የያዝነውን የልማት እቅድ ስኬታማ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ኮንሰትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው ተቋማቸው ካሁን በፊት እንደእንጦጦ ፓርክ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በአጭር ግዜ መስራት የቻለ ተቋም መሆኑን አንስተው ይህንንም ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ  እንዲሁም  ኤጀንሲው ይህን ትልቅ ፋይዳ ያለውን ፕሮጀክት ለማስጀመር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን  ድርሻ እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡ የመገባቢያ ስምምነቱን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እና  የኢትዮጵያ ኮንሰትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የሲቪል መሀንዲሶች ማህበር ፕሬዝዳንት ተፈራረመዋል፡፡

የመደራጀት መብት፣ ሰብዓዊነት፣ የኅብረተሰቡ የላቀ ተጠቃሚነት!!!

የሲ.ማ.ድ.ኤ የኮሚኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት