የኤጀንሲው ከፍተኛ አመራሮች ሰላም የህጻናት መንደርን ጎበኙ፡፡ ሰላም የህጻናት መንደር በወ/ሮ ጸሐይ ሮሲሊ አማካይነት እ.ኤ.አ በ1986 ከወሎ በድርቅ ምክንያት የተቸገሩ ህጻናትን በማምጣት መቋቋሙን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሰለሞን ጫሊ ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ ወላጅ አልባ ህጻናትን እና የተጎዱ ቤተሰቦችን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚ ማረግ እና ስብዕናቸው የተሟላ ትውልድ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ልጆች ላይ የዘሩት ለትውልድ ይተርፋል!! የሚል መሪ ቃል ያለው በህጻናት፣ወጣቶችና ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በድርጅቱ ከተካተቱ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሰላም ቴክኒክና ሞያ ማሰልጠኛ ተቋም አንዱ ሲሆን በየዓመቱ በርካታ ወጣቶችን በተለያየ ሙያ በማሰልጠን ለ90 ፐርሰንቱ የስራ ዕድል መፍጠሩ ከሌሎች ቴክኒክና ሞያ ተቋም እንደሚለየው ከገለጻው ለመረዳት ችለናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እናቶች ልጆቻቸውን በማቆያ እንዲውሉ በማድረግ የራሳቸውን ገቢ እንዲያሳድጉ እና ህጻናቱም በቆይታቸው በቂ ምግብ እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲሆን አሁን ላይ 150 ህጻናት በዚህ አገልግሎት ከድርጅቱ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ የትምህርት፣የስኮላርሽፕ አድል፣የህክምና፣የሙያ ስልጠና፣ የብድር አገልግሎት፣የስራ እድል ትስስር መፍጠር፣የህጻናት ማቆያ እና በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት በማቆያው ቤተሰባዊ ስሜትና ሃላፊነት ተሰምቷቸው ብሎም በስነምግባር ታንጸው እንዲያድጉ የሚደረግበት መልካም ተሞክሮ ያለው እና አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት መሆኑ ተብራርቷል፡፡ ድርጅቱ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር አብሮ የሚሰራ ቢሆንም ከዚህ የበለጠ በማስፋፋት ለብዙ ህጻናት ተደራሽ መሆን የሚለውን ግብ ለማሳካት የከብት እርባታ፣የእርሻ ስራ እና ሌሎችም የገቢ ማስገኛ ስራዎችን ይሰራል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት ይህንን ትልቅ ስራ እንድንመለከትና ለዚህ ያበቁት ባለራዕይ እናት ወ/ሮ ጸሐይ ምስጋና ይገባቸዋል በማለት ሰላም የህጻናት መንደር ላይ ሶስቱ የኢኮኖሚ ተዋንያን የሆኑት መንግስት፣የግሉ ዘርፍ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅትን ተመልክቺያለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ይህን ስል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ የተሸከርካሪ ፍቃድ ማረጋገጫ ባለስልጣን ጋር የመንጃ ፍቃድ ስልጠና በመስጠት አብሮ መስራቱ፣ለተማሪዎቹ የስራ አድል ለመፍጠር ከግል ካንፓኒዎች ጋር መቀናጀቱ እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር መስራቱ ማሳያ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ድርጅቱ ብዙ ለሃር የሚጠቅም ፕሮጀክትን ይዞ እየሰራ የሚገኝ መሆኑን በመግለጽ ሃገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በጎ ማድረግ አስፈላጊ ነው ፡፡ በጎ ስራ የሰሩ እና እየሰሩ ያሉ ሰዎች እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ በመሆናቸው ስራቸው ለአዲሱ ትውልድ ሊነገር ይገባል ይህንን ደግሞ ለማድረግ መንግስትም ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡