የከበረ ዝግባ ቀንበጥ የበጎ አድራጎትና የልማት ድርጅት ከአዲስ አበባ 70 ኪሎሜትር ላይ በምትገኘው ውጫሌ ወረዳ ይገኛል፡፡ የመስክ ምልከታውን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ የሆፕ ቸስት ቺልድረንስ (children’s hope chest) የስራ ሃላፊዎችና ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ከመጡ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ድርጅቱን ጎብኝተዋል ፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ስለድርጅት አመሰራረት ገለፃ ያደረጉልን የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሪት ስምረት መንገሻ እንዳሉት ድርጅቱ ሲቋቋም ዓላማ አድርጎ የተነሳው ወላጅ አልባ የሆኑትና ለጥቃት የተጋለጡ ህፃናት የትምህርት፣ የምግብ፣ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ቤተሰባቸውን፣ ህብረተሰባቸውን እንዲሁም ሀገራቸውን የሚወዱና በራሳቸው ሚተማመኑ፣ ሃላፊነት የሚሰማቸው፣ ከጥገኝነት ነፃ ሆነው እንዲያድጉ ለማድረግ ተብሎ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ስራ አስኪያጇ አክለውም ድርጅቱ በአሁን ጊዜ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ከ50 በላይ ህፃናትን በስሩ አቅፎ በጤናና በትምህርት ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ በመግለፅ በተጨማሪም ከ120 በላይ የሆኑ ህፃናትን ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው በትምህርትና በጤና አገልግሎት ድጋፍ እያደረጉላቸው እንዳለም ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም የአካባቢውን ህብረተሰብ ከልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በጥምረት በመስራት  ቺልድረንስ ሆፕ ቸስት (children’s hope chest) ከተባለው የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት በተገኘ ፈንድ  የንፁህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ በማስቆፈር ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ያስረዳሉ፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ራሱን ለመቻል በገቢማስገኛ ስራ ላይ ከቺልድረንስ ሆፕ ቸስት (children’s hope chest) በተገኘ ድጋፍ በሰፊው በመሳተፍ ላይ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ ስምረት በንብ ማነብ፣የወተት ላሞችን በማርባት ፣በጎችን በማርባት፣የእንቁላል ዶሮችንና የዘይት መጭመቂያ ስራላይ በመሰማራት እንዲሁም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማምረት ገቢውን ማሳደግ እንደቻሉና በቀጣይም ይህንኑ በማጠናከር በርካታ ስራዎችን ለመስራት ድርጅቱ ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል ፡፡

በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት በተቋሙ እየተሰሩ ያሉት ስራዎችን በማድነቅ እየሰራችሁ ያለው ስራ በተለይም ድርጅቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ከጠባቂነት መንፈስ ለመውጣት በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ እየሰራችሁ ያለው ተግባራት የሚደነቅና የሚበረታታ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ለጋሽ ድርጅቶችም ቢሆኑ እንዴት አድርገን ከችግር ውስጥ መውጣት እንደምንችል መንገድ እንዲያሳዩን እንጂ እስከ ህይወት ዘመናችን እንዲረዱን መፍቀድ አይኖርብንም ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ ራሱን ለመቻልና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ እየሰራ ያለው ስራ ትልቅ ማሳያ መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ለድርጅቱ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም የአገራችን እድገት የሚረጋገጠው መንግስት፣ የግሉ ሴክተር እና የሲቪል ማህበረሰቡ  ትስስር ሲፈጥር ነው፡፡ ይህንን ካደርግንና ሁላችንም የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ከተወጣን የህብረተሰባችንን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የማንችልበት እንዲሁም ከልመናም የማንላቀቅበት ምክንያት አይኖርም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡