የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የአሰራር ዘይቤውን በመቀየር ቀደም ሲል በወረቀት ይሰጥ የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ከአርባ አምስት በላይ በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶችን  በኢ-ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልፀ፡፡

በተቋሙ ውስጥ አገልግሎቱን ለመጀመር ለተቋሙ ባለሙያዎችና ሃላፊዎች በአገልግሎት አሰጣጡና በአጠቃቀሙ ዙርያ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የተቋሙን ባለሙያዎች ሲያዘጋጅ እንደቆየ ይታወሳል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስለ አገልግሎቱ አጠቃቀምና በአገልግሎቱ ስለተካተቱ የተቋሙ አገልግሎቶች በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ገለጻ አድርገጓል፡፡

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት ላለፉት ሶስት ዓመታት በሃገራችን በነበረው የለውጥ ሂደት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሁለተናዊ ብልፅግና ላይ የራሳቸውን ሚና መጫወት እንዲችሉ ህግና ተቋማዊ ሪፎርሞች መካሄዳቸውን በማስታወስ በቅርቡም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር የመንግስት አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ እንዲሰጡ ለማድረግ በጀመረው እንቅስቃሴ መሰረት ኤጀንሲያችን የኢ-ሰርቪስ አገልግሎትን በማስጀመር ተቋማችን ወደ ተሻለ የአገለግሎት አሰጣጥ እንዲሸጋገር በማድረግ የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር የአይ ሲቲ ልማት ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ኢንጂነር አብዮት ሲናሞ በበኩላቸው በሃገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ወደፊት እንዲራመድ ለማድረግ ባለፉት አመታት የሃገሪቱ የኢ ትራንዛክሽን አዋጅ ፀድቆ ስራ ላይ መዋሉ ይታወሳል፤ ይህም በዋናነት ቀደም ሲል በወረቀት ይሰሩ የነበሩ አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ ቢሰሩ ህጋዊነታቸውን አያጡም የሚል መሰረታዊ የህግ ማዕቀፍ ማስቀመጡን ገልጸዋል ፡፡ አያይዘውም በዚህ የህግ ማዕቀፍ መሰረት የ E_government ስራዎች ማለትም መንግስት ከዜጎች፣ መንግስት ከንግዱ ማህበረሰብ ወይም የመንግስት ተቋማት ከመንግስት ተቋማት ጋር የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች በሂደት ወደ ኤሌክትሮኒክስ መጠቀሚያ ዘዴ እንዲቀየሩ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል ፡፡

በአገልግሎቱ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ቴክኖሎጂው ጊዜንና ጉልበትን በመቆጠብ ያላስፈላጊ እንግልትን የሚያስቀር መሆኑን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ የመንግስት ተቋማት አገልግሎታቸውን ዲጂታል በማድረግ የኢ ሰርቪስ አገልግሎት እንዲሰጡ ከተመረጡ 20 የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አንዱ ሲሆን በተቋሙ የሚሰጡ አርባ አምስት አገልግሎቶች በኢ ሰርቪስ የሚሰጡ ይሆናል፡፡ በአገልግሎቱ ላይ  የሚነሱ አስተያየቶች ካሉም ለኤጀንሲው ማሳወቅ የሚቻል መሆኑም ታውቋል፡፡