የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ደቡብ ወሎ ዞን የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራን ጀመረ፡፡

የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በደቡብ ወሎ ዞን 037 ቀበሌ ለአራት መቶ ተማሪዎች የትምህት ቁሳቁስ ድጋፍ፣የችግኝ ተከላ መርሃግብር እና በቀጣይ ለሚያስገነባቸው የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የማኖር መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡ በመርሃግብሩ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ፣ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ፣አቶ ተስፋ ዳኘው የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ጽ/ቤት ሃላፊ ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በመክፈቻ ንግግራቸው ባስተላለፉት መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ የተጀመረ ብሔራዊ ንቅናቄ መሆኑን በመግለጽ በጎ ፈቃድ ሥራ ገንዘብ ሳይሆን ጊዜያችን፣ ጉልበታችን፣ እውቀታችን እና ፍቅራችን የምናጋራበት እና የምንሰራው ትንሽ ስራ በሌላ ሰው ሕይወት ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ተግባር በመሆኑ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከዚህ አንጻር በጎ ፈቃድ ሥራ የዛሬን ችግር ብቻ የሚፈታ ሳይሆን የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት ባህልን በማጠናከር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሠረት የሚጥል ተግባር በመሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጉልህ ተሳተፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ።

አያይዘውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገራችን የልማት፣ የሰላም፣ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የዜጎች ተሳትፎ ማጎልበት ውስጥ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ሁሉ በጎ ፈቃደኝነትም ከእነዚህ እሴቶች የሚመነጭ ተግባራዊ መገለጫ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በማለት ለዚህ ፕሮግራም መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የዞኑ የስራ ሃላፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋ ዳኘው በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት በክረምት የበጎ ፍቃድ ስራ ሶስት ግቦችን በማስቀመጥ አቅዶ እየሰራ መሆኑን በመግለጽ በዘንድሮ በጀት ዓመት ብቻ 1276 የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ ለማከናወን አቅደው ከጅምሩ 326 ቤቶችን ማስገንባት መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሃላፊው እንዳሉት በበጎ ፍቃድ ስራ የውስጥ አቅም፣ የመረዳዳት ባህል እያደገ እና የማህበረሰቡም ችግር እየተቀረፉ መምጣቱን ጠቅሰው ባለስልጣን መስሪያቤቱም ይህንን ተግባር ለማጠናከር በመገኘቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሆለታ አከናወኑ።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች ከእንዳለጌታ የህፃናት መንደር ጋር በመተባበር ”ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሆለታ ከተማ አስተዳደር አከናውኗል። በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህን ጨምሮ የባለስልጣኑ አመራሮችና ሰራተኞች፣ የሆለታ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት ተወካዮች፣ የእንዳለጌታ ህፃናት መንደር አባላት እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው መምህራንና ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ቀደም ሲል ሲያደርገው እንደነበረው በዘንድሮውም የክረምት ወቅት የተቋሙን ሰራተኞችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በማስተባበር በርካታ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮችን ለማከናወን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ይህ በተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች የተደረገው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በክረምት በጎ ፈቃድ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ ነው።

በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ላይ የእንዳለው ጌታ የህጻናት መንደር ከሆለታ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው ቦታ ላይ ለህጻናት መንደር ግንባታ አገልግሎት የሚውል ህንፃ ለመገንባት የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው እንዳለውጌታ የህፃናት መንደር ከሆለታ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ወላጅ አልባና አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ፣ በህፃናት ምገባ እና ድጋፍ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው። ህፃናት እና አረጋውያንን ማዕከል በማድረግ በሆለታ ከተማ የተሰሩ ፕሮጀክቶችን የድርጅቱ መስራችና ስራአስኪያጅ አቶ እንዳለውጌታ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አስጎብኝተዋል።


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ የስትሮክ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ የስትሮክ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ለተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናና የስትሮክ ምርመራ ተደርጓል። በመርሀ ግብሩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ስትሮክ ፋውንዴሽን የስራ ሀላፊዎች እና የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ ለህክምና ቡድኑና ለፋውንዴሽኑ አመራሮች እንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ወደፊትም ከድርጅቱ ጋር በትብብርና በአጋርነት ላይ ተመስርተው ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ስትሮክ ፋውንዴሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ሻሎም ያዕቆብ በበኩላቸው ድርጅታቸው በስትሮክ ተጠቂ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የህክምና ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ለማህበረሰቡ ስለስትሮክ ግንዛቤ መፍጠርና በስትሮክ ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን ማድረግ እንዲሁም ባለሙያዎችን ማብቃት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። አያይዘውም ስትሮክ በጊዜ ከተደረሰበት መከላከልና መዳን እንደሚችል ነገር ግን ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ በርካቶች በቂ ክትትልና ቅድመ መከላከል ባለማድረጋቸው ለችግሩ ተጋላጭ እየሆኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱና በዘርፉ ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ሻሎም ያዕቆብ አክለዋል።

የባለስልጣን መስሪያቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሲካው ሞላ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጽት የሰራተኞችን ደህነትና ጤንነት ለመጠበቅ በርካታ ስራዋች እንደሚሰሩ ገልጸው የዚሁ አካል የሆነውን የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ለሰራተኞች ነጻ የምርመራ ዕድል ለሰጠን የኢትዮጵያ ስትሮክ ፍውንዴሽን ምስጋና ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፍዋል። የህክምናና የማማከር አገልግሎቱን በፋውንዴሽኑ ባለሙያዎች ለግማሽ ቀን የተሰጠ ሲሆን ስትሮክን በተመለከተ የግንዝቤ ማስጨበጫ በዘርፉ ባለሙያ ቀርቧል።


በፍትህ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የተገነቡ 18 የመኖርያ ቤቶች የምረቃና ርክክብ ስነስርዓት ተከናወነ።

በምስራቅ መሰቃንና ማረቆ ወረዳዎች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡና ለአቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንዲውሉ ታስበው የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶች የፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር ወ/ሮ ሀና አርዓያሥላሴን ጨምሮ የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎችና የዞንና የወረዳ አመራሮች እና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ የማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የምረቃና የማስተላለፍ ስነስርዓት ተካሂዷል።

በፍትህ ሚንስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ተገንብተው ለምረቃ የበቁት ምስራቅ ምስቃን ወረዳ 9 እንዲሁም በማረቆ ልዩ ወረዳ 9 በድምሩ 18 የመኖሪያ ቤቶች ሲሆኑ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ 18 አባዎራዎች በፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር ወ/ሮ ሀና አርዓያሥላሴ አማካኘነት ተመርቀዋል፡፡ከተመረቁት 18 የመኖሪያ ቤቶች 14ቱ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሙሉ ክትትልና ድጋፍ ተደርጎባቸው ለምረቃ የበቁ ሲሆን ቀሪዎቹ 4 የመኖሪያ ቤቶች ደግሞ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ሙሉ ክትትልና ድጋፍ ተደርጎባቸው ተገንብተዋል፡፡

በርክክብ መርኃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር ወ/ሮ ሀና አርዓያሥላሴ እንደገለጹት ሀገር የምትጸናው በልጆቿ ትጋትና ርብርብ መሆኑን ጠቅሰው ለተቋም ከሚሰራው ስራ ባለፈ ለማህበረሰቡ በተጨባጭ በምናስመዘግበው ውጤት በመሆኑ በከፍተኛ ትጋትና ቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኘና በይፋ የተመረቁት የመኖሪያ ቤቶችም ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ክብርት ሚኒስትሯ አክለውም በወረቀት ከሚቀርቡ ትልልቅ እቅዶች ባለፈ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ፤ ተጀምረው የሚጠናቀቁ ስራዎችን በመስራት የህዝባችንን ተጠቃሚነት ማሻሻል ይኖብናል ብለዋል፡፡ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይመለከተናል በሚል መንፈስ በመፈጸም ወደፊት ለሚሰሩ በጎ ስራዎች ሰፊ መሠረት ለመጣል መሆኑን ጠቁመው ለዚህ በጎ ስራ አስተዋፅዖ ላደረጉ ተቋማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካዔል በበኩላቸው ሀገራችን ውስጥ የነበሩ የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ፣ የአብሮነትና የመጠያያቅ እሳቤዎች ለሰላምና መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽዖ ያላቸው በመሆኑ ይህን እሳቤ በማሳደግ ብዙ ችግሮቻችንን መቅረፍ እንችላለን ብለዋል፡፡

አክለውም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በቁሊቶ ከተማ መጀመሩን በማስታወስ በዘንድሮው ዓመትም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና የአቅመ ደካማ ቤቶችን በመገንባት የተጀመሩ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ለማስቀጠል እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡በፍትህ ሚንስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ አስተባባሪነት በሁለቱ ወረዳዎች ያስተላለፍናቸው ቤቶች በከፍተኛ ችግር ውስጥ የነበሩ እና በስራቸው ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ትልቅ እፎይታን የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው ለዚህ ስኬት ጉልህ ድርሻ የነበራቸውን ተቋማት አመስግነዋል፡፡ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ ላበረከቱ የመንግስት ተቋማት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምስጋና የምስክር ወረቀት ከሁለቱም ወረዳዎች የተበረከተ ሲሆን ቤት ለተገነባላቸው አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች የቁልፍ ርክክብም ተደርጓል፡፡


በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስተባባሪነት በትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ድርጅቶች ልምድ ልውውጥ ተደረገ።

በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስተባባሪነት በትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ድርጅቶች ልምድ ልውውጥ ተደረገ።

ምናልባት የአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች እና የሚያጠኑ ሰዎች ምስል
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በስሩ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውጤታማ ስራዎችን ሰርተው ሀገርንና ማህበረሰቡን በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችሉ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። ይህንኑ ተከትሎ በትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩት የሳንፎርድና ቀለም ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች ደብረ ብርኃን ከተማ ከሚገኘውና በምዝገባ ሂደት ላይ በሚገኘው የሀይሌ ማናስ አዳሪ ትምህርት ቤት ተገኝተው የልምድ ልውውጥ አድርገዋል። የልምድ ልውውጡ በትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ የዘለቄታ በጎ አድራጎት (charity endowment) ድርጅቶች ውጤታማና ብቁ የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆችን ለማፍራት ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥራትንና ውጤታማነትን መሠረት ያደረገ ትምህርት በመስጠት አሰራራቸውን እንዲያዘምኑና የተቋቋሙበት አላማ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን እገዛ የሚያደርግ ነው።ሀይሌ ማናስ አካዳሚ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ የአዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን በስሩ ከ260 በላይ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ተማሪዎችን ይዞ በማስተማር ላይ የሚገኝ የትምህርት ተቋም ነው። አካዳሚው ዘመናዊ እና እጅግ የተሟላ መሠረተ ልማት የያዘ ሲሆን የሀገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ ተከትሎ ውጤታማ ተማሪዎችን እያፈራም ይገኛል። በቅርቡም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ቀርቦ የምዝገባ ሂደቱን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን አካዳሚው ውጤታማነቱን በማስቀጠል ህብረተሰቡን በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ ለማድረግ በጥረት ላይ ይገኛል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አካዳሚው እየተከተለው ያለው የትምህርት አሰጣጥ ለሌሎች መሠል ተቋማት ከልምድ አንጻር ያለውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ቀለም እና ሳንፎርድ ያሉ ሀገር በቀል የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ አስችሏል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡበት ነው -አቶ አደም ፋራህ

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋገጡበት ነው -አቶ አደም ፋራህ

 

ምናልባት የአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች እና ከፍ ያለ መድረክ ምስል

አዲስ አበባ ፤ሰኔ 6 /2018 (ኢዜአ) ፦ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጡበት መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለተሳተፉና አዎንታዊ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት፤ ምክር ቤቱ ምርጫው በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት ላዘጋጀው የዕውቅና መርሐ ግብር ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
የተቋም ግንባታ የሥልጣኔ መገለጫ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አደም ፋራህ፤ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው የሕልውና እና የብልፅግና መሠረት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ዴሞክራሲ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የምንገነባበት ምሰሶ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት አቶ አደም፤ ሀገራዊ ተቋማትን በጋራ ጥረትና መሥዋዕትነት መገንባት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በምርጫው ወቅት የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ዜጎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ፅኑ ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳየበት መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በምርጫው ወቅት የነበረውን ንቁ ተሳትፎ አድንቀው፤ በተለይም ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ድርጅቶቹ ገንቢ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የሲቪክ ማኅበራት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ሚና እንዲያሳድጉ ሰፊ ሥራ መሠራቱን የጠቀሱት አቶ አደም፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የታየው ከፍተኛ ተሳትፎም ያለፈው ጥረታችን ውጤት ነው ብለዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ይበልጥ ለማጠናከርና አጋርነታቸውን ለማስቀጠል መንግሥት ሙሉ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በፖለቲካው ምኅዳር በፉክክርና በትብብር መካከል ያለውን ሚዛን ጠብቆ የመሄድ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከሥጋት ቀጣና ወጥተው ወደ እውነተኛ የልማት አጋርነት ተሸጋግረዋል ::

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከሥጋት ቀጣና ወጥተው ወደ እውነተኛ የልማት አጋርነት ተሸጋግረዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከቀድሞ የሥጋትና የጥርጣሬ ቀጣና ወጥተው ወደ እውነተኛ የመንግሥት የልማትና የዴሞክራሲ አጋርነት መሸጋገራቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አሕመድ ሁሴን አስታወቁ። የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለተሳተፉና አዎንታዊ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
ምናልባት የከፍ ያለ መድረክ እና 'EGS PIAN ጉጵያ ผ LN Me ሚ9 ህበር CIETY' የሚል ጽሑፍ ምስል
አህመድ ሁሴን የኢትየጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት
"የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ያመሰግናሉ" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፣ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ ሚኒስትሮች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሕዝብን ድምፅ የሚያሰሙና በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የመተማመን ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መሠረታዊ ዓላማቸው የሕዝብን ድምፅ ማስተጋባትና የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል በነበሩ ሕጎች ምክንያት እንደ ሥጋት ታይተው መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በተለይም የአዋጅ ቁጥር 621/2009 መውጣት መንግሥት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ከአጋዥ ይልቅ እንደ ሥጋት እንዲመለከታቸው አድርጎ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ሆኖም ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት ከቁጥጥር ወደ አጋርነት፣ ከገደብ ወደ ትብብር እንዲሸጋገር መደረጉን አብራርተዋል። በዚህም ማህበራቱ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ መቻላቸውን ገልጸዋል። በሰብዓዊ መብትና በማኅበራዊ ተጠያቂነት ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን መሥራታቸውን በመጥቀስ፤ ምርጫ የዴሞክራሲ ፅንሰ-ሐሳብ አንድ አካል መሆኑን ለኅብረተሰቡ ለማስገንዘብ ትልቅ ዕድል ማግኘታቸውንም ተናግረዋል። በዚህም ዜጎች በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ተመልካች ሳይሆኑ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።
የሲቪል ማኅበራት ስኬት የሚለካው ሰላም፣ ልማትና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንዲገነባ በማድረግ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በገለልተኛ ተቋማዊ ብቃት ኃላፊነቱን በአግባቡ ተወጥቷል ብለዋል።
ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የጸጥታ አካላት የነበራቸው ሚና የጎላ እንደነበር በማንሳት፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አማራጭ ሐሳቦችን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ላደረጉት ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረትና ኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎችን በማሰማራት አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ የምስጋና መርሐ ግብሩ የተዘጋጀላቸው የሕግና የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲሁም ሚዲያዎች በሙሉ ትልቅ ክብርና ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ብሔራዊ የማህበራዊ ተጠያቂነት ህብረትን (National Social Accountability Consortium) ለመደገፍና ለማጠናከር የሚረዳ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ተካሄደ።

ብሔራዊ የማህበራዊ ተጠያቂነት ህብረትን (National Social Accountability Consortium) ለመደገፍና ለማጠናከር የሚረዳ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ተካሄደ።
ምናልባት የአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች፤ ከፍ ያለ መድረክ እና ጽሑፍ ምስል
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከብሔራዊ የማህበራዊ ተጠያቂነት ህብረት (National social Accountability Consortium ጋር በመተባበር የዲጂታል ተጠያቂነትንና አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል (Excel Digital Accountability and service delivery) በሚል መሪ ሀሳብ ከብሔራዊ የማህበራዊ ተጠያቂነት ህብረት አባላትና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከማህበረሰብ ተወካዮች ጋር የውይይት መድረክ ያካሄደ ሲሆን መድረኩ የተዘጋጀው የህብረቱን አባላትና ባለድርሻ አካላትን አቅም ለማሳደግና ለመደገፍ ያለመ ነው። በውይይቱ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱን ጨምሮ የህብረቱ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እና የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።
በመድረኩ ላይ የማህበራዊ ተጠያቂነትን ለማሳለጥ ይረዳ ዘንድ በህብረቱ የበለፀገውን የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ገጽ (Ethiopian Social Accountability platform) በሚመለከት ገለጻ የተደረገ ሲሆን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ አማካኝነት የዲጂታል ገጽ ርክክብ ተደርጓል።
የተለያዩ ህብረቱን የሚጠናክሩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ህበረቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በሚመለከት ገለጻ ተደርጓል። በተጨማሪም በሰላም ሚኒስቴር የሰላም አደረጃጀቶች ሚና በሚል ርዕስ የሰላም እሴቶች በማህበረሰብ ደረጃ እንዲሰርጹ ማድረግን ዓላማ ያደረገ የውይይት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በፌደራል መንግስት የግዢ አፈጻጸም መመሪያ ላይ ለተቋሙ የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ፡፡

በፌደራል መንግስት የግዢ አፈጻጸም መመሪያ ላይ ለተቋሙ የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ፡፡

በስልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ባስተላለፉት መልዕክት ባለስልጣን መስሪያቤቱ ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ ከሚያስችሉ ቁልፍ ተግባራት ውስጥ ግልጽነትን ማጠናከር እና በተቋሙ ውስጥ የመልካም አስተዳደር እሴቶችን ማጎልበት ቀዳሚ ስፍራ የሚይዙ መሆናቸውን በመግለጽ ይህንን ግብ ለማሳካት ሁሉም አመራርና ባለሙያ ከግዢና ንብረት አስተዳደር ጋር የተያያዙ አዋጆችን መመሪያዎችንና ስርዓቶችን በበቂ ሁኔታ በመረዳት ተግባር ላይ ማዋል ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ይህ ስልጠና የሕጉን ይዘት ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ በሥራችን ውስጥ የሚገጥሙንን ተግባራዊ ጉዳዬች በሕግ እና በአሰራር መሰረት ለመፍታት የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት ለማጎልበት ጭምር መሆኑን በመጥቀስ በስልጠናው የሚቀርቡ ጽንሰ-ሐሳቦችን፣የሕግ ድንጋጌዎችን እና የተግባር ልምዶችን በጥልቀት በመወያየት ለተቋማችን የተሻለ የአሰራር ባህል ለመገንባት እንጠቀማለን ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ውጤታማ የግዢና ንብረት አስተዳደር ማለት ህግን ማክበር ብቻ ሳይሆን የህዝብ ሀብት በኃላፊነት መጠቀም ብክነትን መከላከል፣ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና ለተቋሙ ዘላቂ ተቋማዊ አቅም መፍጠር ማለት ጭምር መሆኑን አብራርተው ሁሉም ሰራተኛ የሥራ ዘርፍ ሕጋዊነትን፣ተጠያቂነትን እና ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በጽናት እንድናሰፈን ይጠበቃል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የባለስልጣን መስሪያቤቱ የስነምግባር መከታተያ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጸሐይ ሽፈራው ባስተላለፉት መልዕክት የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት የመንግስት ተቋማት ተልዕኳቸውን በብቃት፣በታማኝነትና ተጠያቂነት እንዲፈጽሙ ከሚያስችሉ ዋና ዋና የአስተዳደር ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የግዢ ሂደቶች በሕግ መሰረት መመራታቸውን፣የመንግስት ሀብት በአግባቡ መጠበቁንና መተዳደሩ እንዲሁም የህዝብ ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ ለማዋል እንደዚህ ዓይነት ስልጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ስልጠናውን ከግዢ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመጡ ባለሙያዎች  ሰጥተዋል፡፡


ሎካላይዜሽን ራስን የመቻል አንድ እርምጃ!

ሎካላይዜሽን ራስን የመቻል አንድ እርምጃ!

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከእለት ወደእለት ወደከፍታ ማማ እየተመነደገ ነው። መፃኢው ዘመን የኢትዮጵያ የትሩፋት ዘመን እንዲሆን ያለ እረፍት በትጋት መስራት፤ በሁሉም ዘርፍ እራስን መቻል የቅድሚ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ሎካላይዜሽን ራስን የመቻል አንድ እርምጃ ነው ሲባል እራስ በራስ ከማስተዳደርና የሀብት ምንጭን በማስፋት ራስን ከመቻል ባለፈ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በዘላቂነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም ከተረጂነት እንዲላቀቁ ማድረግ ነው::

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሀገራችንን የያዘችውን በሁሉም ዘርፍ የመበልፀግ ውጥን እውን ለማድረግ በሲቪል ማህበራት ዘርፍ በሚጠበቅበት ልክ ሚናውን እንዲወጣ በትጋት እየሰራ ይገኛል። የሲቪል ማህበራት የውጪ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ከመሆን ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ እንዲሁም ህብረተሰቡ በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ህግንና መርህን መሰረት አድርገው ተንቀሳቅሰው መንግስትና ህዝብ የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እንዲሁም ሀገሪቱ የምትፈልገውን የልማትና የዲሞክራሲ ግንባታ ለመደገፍ ድርሻቸው የጎላ መሆን ይኖርበታል።

የዘርፉን ሚና የበለጠ ከፍ ለማድረግ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ከነዚህ እርምጃዎች አንዱ የሎካላይዜሽን ኢኒሼቲቭ ነው። ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ነሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በራስ አቅም የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ከመደገፍ ባሻገር በፖሊሲ እንዲደገፉ እና በህግ እንዲመሩ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሎካላይዜሽን ጽንሰ ሀሳብ በዘርፉ እንዲሰርጽ በማድረግ በፖሊሲ ማዕቀፍ የታገዘ የሶሻል ኢንተርፕራይዝ እንዲኖር እንዲሁም የበጎ ፈቃድና በጎ አድራጊነት ባህል እንዲሰርፅ በትጋት እየሰራ ይገኛል።

በተለይም ከሶሻል ኢንተርፕራይዝ ጋር በተያያዘ የአስቻይ ሁኔታ ቅድመ ጥናት በማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለዘርፉ አመቺ የፖሊሲ ማዕቀፍ ለማበጀት የሚያስችል የፖሊሲ ጥናት በማድረግ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም የሲቪል ማህበራት ከፈንድ እና ከህዝባዊ መዋጮዎች ወጥተው የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት ስራዎቻቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል መመሪያ በመቅረፅ የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሰፉ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለይም በአሁኑ ጊዜ ሁሉን አቀፍ ራስን የመቻል ትልሟ እንዲሳካ በየዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ ራስን የመቻል መርህን የተከተሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

 

ሀገራችን የያዘችው የልማት ውጥን ፍሬያማ እንዲሆን የሲቪል ማህበራት ድርሻ የጎላ መሆኑን ተገንዝበው በልማት፣ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዱሁም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ሁሉን አቀፍ ተግባራት ሁሉ ህግንና የህብረተሰቡን እሴት ባከበረ መልኩ ከመቼውም በበለጠ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በዘርፉ የሚታዩ እመርታዎች የበለጠ ፍሬያማ እንዲሆኑ የሚደረጉ ድጋፎችና ክትትሎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።