በምስራቅ መሰቃንና ማረቆ ወረዳዎች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡና ለአቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንዲውሉ ታስበው የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶች የፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር ወ/ሮ ሀና አርዓያሥላሴን ጨምሮ የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎችና የዞንና የወረዳ አመራሮች እና የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ የማህበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የምረቃና የማስተላለፍ ስነስርዓት ተካሂዷል።

በፍትህ ሚንስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ተገንብተው ለምረቃ የበቁት ምስራቅ ምስቃን ወረዳ 9 እንዲሁም በማረቆ ልዩ ወረዳ 9 በድምሩ 18 የመኖሪያ ቤቶች ሲሆኑ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ 18 አባዎራዎች በፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር ወ/ሮ ሀና አርዓያሥላሴ አማካኘነት ተመርቀዋል፡፡ከተመረቁት 18 የመኖሪያ ቤቶች 14ቱ ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሙሉ ክትትልና ድጋፍ ተደርጎባቸው ለምረቃ የበቁ ሲሆን ቀሪዎቹ 4 የመኖሪያ ቤቶች ደግሞ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ሙሉ ክትትልና ድጋፍ ተደርጎባቸው ተገንብተዋል፡፡

በርክክብ መርኃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር ወ/ሮ ሀና አርዓያሥላሴ እንደገለጹት ሀገር የምትጸናው በልጆቿ ትጋትና ርብርብ መሆኑን ጠቅሰው ለተቋም ከሚሰራው ስራ ባለፈ ለማህበረሰቡ በተጨባጭ በምናስመዘግበው ውጤት በመሆኑ በከፍተኛ ትጋትና ቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኘና በይፋ የተመረቁት የመኖሪያ ቤቶችም ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ክብርት ሚኒስትሯ አክለውም በወረቀት ከሚቀርቡ ትልልቅ እቅዶች ባለፈ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ፤ ተጀምረው የሚጠናቀቁ ስራዎችን በመስራት የህዝባችንን ተጠቃሚነት ማሻሻል ይኖብናል ብለዋል፡፡ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይመለከተናል በሚል መንፈስ በመፈጸም ወደፊት ለሚሰሩ በጎ ስራዎች ሰፊ መሠረት ለመጣል መሆኑን ጠቁመው ለዚህ በጎ ስራ አስተዋፅዖ ላደረጉ ተቋማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካዔል በበኩላቸው ሀገራችን ውስጥ የነበሩ የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ፣ የአብሮነትና የመጠያያቅ እሳቤዎች ለሰላምና መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽዖ ያላቸው በመሆኑ ይህን እሳቤ በማሳደግ ብዙ ችግሮቻችንን መቅረፍ እንችላለን ብለዋል፡፡ 
አክለውም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በቁሊቶ ከተማ መጀመሩን በማስታወስ በዘንድሮው ዓመትም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና የአቅመ ደካማ ቤቶችን በመገንባት የተጀመሩ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ለማስቀጠል እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡በፍትህ ሚንስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ አስተባባሪነት በሁለቱ ወረዳዎች ያስተላለፍናቸው ቤቶች በከፍተኛ ችግር ውስጥ የነበሩ እና በስራቸው ለሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ትልቅ እፎይታን የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው ለዚህ ስኬት ጉልህ ድርሻ የነበራቸውን ተቋማት አመስግነዋል፡፡ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ ላበረከቱ የመንግስት ተቋማት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምስጋና የምስክር ወረቀት ከሁለቱም ወረዳዎች የተበረከተ ሲሆን ቤት ለተገነባላቸው አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች የቁልፍ ርክክብም ተደርጓል፡፡

