ሎካላይዜሽን ራስን የመቻል አንድ እርምጃ!
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከእለት ወደእለት ወደከፍታ ማማ እየተመነደገ ነው። መፃኢው ዘመን የኢትዮጵያ የትሩፋት ዘመን እንዲሆን ያለ እረፍት በትጋት መስራት፤ በሁሉም ዘርፍ እራስን መቻል የቅድሚ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ሎካላይዜሽን ራስን የመቻል አንድ እርምጃ ነው ሲባል እራስ በራስ ከማስተዳደርና የሀብት ምንጭን በማስፋት ራስን ከመቻል ባለፈ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በዘላቂነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም ከተረጂነት እንዲላቀቁ ማድረግ ነው::

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሀገራችንን የያዘችውን በሁሉም ዘርፍ የመበልፀግ ውጥን እውን ለማድረግ በሲቪል ማህበራት ዘርፍ በሚጠበቅበት ልክ ሚናውን እንዲወጣ በትጋት እየሰራ ይገኛል። የሲቪል ማህበራት የውጪ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ከመሆን ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ እንዲሁም ህብረተሰቡ በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ህግንና መርህን መሰረት አድርገው ተንቀሳቅሰው መንግስትና ህዝብ የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እንዲሁም ሀገሪቱ የምትፈልገውን የልማትና የዲሞክራሲ ግንባታ ለመደገፍ ድርሻቸው የጎላ መሆን ይኖርበታል።
የዘርፉን ሚና የበለጠ ከፍ ለማድረግ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ከነዚህ እርምጃዎች አንዱ የሎካላይዜሽን ኢኒሼቲቭ ነው። ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ነሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በራስ አቅም የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ከመደገፍ ባሻገር በፖሊሲ እንዲደገፉ እና በህግ እንዲመሩ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሎካላይዜሽን ጽንሰ ሀሳብ በዘርፉ እንዲሰርጽ በማድረግ በፖሊሲ ማዕቀፍ የታገዘ የሶሻል ኢንተርፕራይዝ እንዲኖር እንዲሁም የበጎ ፈቃድና በጎ አድራጊነት ባህል እንዲሰርፅ በትጋት እየሰራ ይገኛል።
በተለይም ከሶሻል ኢንተርፕራይዝ ጋር በተያያዘ የአስቻይ ሁኔታ ቅድመ ጥናት በማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለዘርፉ አመቺ የፖሊሲ ማዕቀፍ ለማበጀት የሚያስችል የፖሊሲ ጥናት በማድረግ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም የሲቪል ማህበራት ከፈንድ እና ከህዝባዊ መዋጮዎች ወጥተው የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት ስራዎቻቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያስችል መመሪያ በመቅረፅ የገቢ ምንጫቸውን እንዲያሰፉ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለይም በአሁኑ ጊዜ ሁሉን አቀፍ ራስን የመቻል ትልሟ እንዲሳካ በየዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ ራስን የመቻል መርህን የተከተሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
ሀገራችን የያዘችው የልማት ውጥን ፍሬያማ እንዲሆን የሲቪል ማህበራት ድርሻ የጎላ መሆኑን ተገንዝበው በልማት፣ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዱሁም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ሁሉን አቀፍ ተግባራት ሁሉ ህግንና የህብረተሰቡን እሴት ባከበረ መልኩ ከመቼውም በበለጠ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በዘርፉ የሚታዩ እመርታዎች የበለጠ ፍሬያማ እንዲሆኑ የሚደረጉ ድጋፎችና ክትትሎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

