የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ የስትሮክ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ለተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናና የስትሮክ ምርመራ ተደርጓል። በመርሀ ግብሩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ስትሮክ ፋውንዴሽን የስራ ሀላፊዎች እና የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ ለህክምና ቡድኑና ለፋውንዴሽኑ አመራሮች እንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ወደፊትም ከድርጅቱ ጋር በትብብርና በአጋርነት ላይ ተመስርተው ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ስትሮክ ፋውንዴሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ሻሎም ያዕቆብ በበኩላቸው ድርጅታቸው በስትሮክ ተጠቂ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የህክምና ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ለማህበረሰቡ ስለስትሮክ ግንዛቤ መፍጠርና በስትሮክ ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን ማድረግ እንዲሁም ባለሙያዎችን ማብቃት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። አያይዘውም ስትሮክ በጊዜ ከተደረሰበት መከላከልና መዳን እንደሚችል ነገር ግን ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ በርካቶች በቂ ክትትልና ቅድመ መከላከል ባለማድረጋቸው ለችግሩ ተጋላጭ እየሆኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱና በዘርፉ ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ሻሎም ያዕቆብ አክለዋል።

የባለስልጣን መስሪያቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሲካው ሞላ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጽት የሰራተኞችን ደህነትና ጤንነት ለመጠበቅ በርካታ ስራዋች እንደሚሰሩ ገልጸው የዚሁ አካል የሆነውን የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ለሰራተኞች ነጻ የምርመራ ዕድል ለሰጠን የኢትዮጵያ ስትሮክ ፍውንዴሽን ምስጋና ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፍዋል። የህክምናና የማማከር አገልግሎቱን በፋውንዴሽኑ ባለሙያዎች ለግማሽ ቀን የተሰጠ ሲሆን ስትሮክን በተመለከተ የግንዝቤ ማስጨበጫ በዘርፉ ባለሙያ ቀርቧል።