የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች ከእንዳለጌታ የህፃናት መንደር ጋር በመተባበር ”ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሆለታ ከተማ አስተዳደር አከናውኗል። በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህን ጨምሮ የባለስልጣኑ አመራሮችና ሰራተኞች፣ የሆለታ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት ተወካዮች፣ የእንዳለጌታ ህፃናት መንደር አባላት እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው መምህራንና ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ቀደም ሲል ሲያደርገው እንደነበረው በዘንድሮውም የክረምት ወቅት የተቋሙን ሰራተኞችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በማስተባበር በርካታ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮችን ለማከናወን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ይህ በተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች የተደረገው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በክረምት በጎ ፈቃድ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ ነው።

በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ላይ የእንዳለው ጌታ የህጻናት መንደር ከሆለታ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው ቦታ ላይ ለህጻናት መንደር ግንባታ አገልግሎት የሚውል ህንፃ ለመገንባት የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው እንዳለውጌታ የህፃናት መንደር ከሆለታ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ወላጅ አልባና አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ፣ በህፃናት ምገባ እና ድጋፍ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው። ህፃናት እና አረጋውያንን ማዕከል በማድረግ በሆለታ ከተማ የተሰሩ ፕሮጀክቶችን የድርጅቱ መስራችና ስራአስኪያጅ አቶ እንዳለውጌታ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አስጎብኝተዋል።