በፌደራል መንግስት የግዢ አፈጻጸም መመሪያ ላይ ለተቋሙ የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ፡፡

በስልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ባስተላለፉት መልዕክት ባለስልጣን መስሪያቤቱ ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ ከሚያስችሉ ቁልፍ ተግባራት ውስጥ ግልጽነትን ማጠናከር እና በተቋሙ ውስጥ የመልካም አስተዳደር እሴቶችን ማጎልበት ቀዳሚ ስፍራ የሚይዙ መሆናቸውን በመግለጽ ይህንን ግብ ለማሳካት ሁሉም አመራርና ባለሙያ ከግዢና ንብረት አስተዳደር ጋር የተያያዙ አዋጆችን መመሪያዎችንና ስርዓቶችን በበቂ ሁኔታ በመረዳት ተግባር ላይ ማዋል ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህ ስልጠና የሕጉን ይዘት ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ በሥራችን ውስጥ የሚገጥሙንን ተግባራዊ ጉዳዬች በሕግ እና በአሰራር መሰረት ለመፍታት የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት ለማጎልበት ጭምር መሆኑን በመጥቀስ በስልጠናው የሚቀርቡ ጽንሰ-ሐሳቦችን፣የሕግ ድንጋጌዎችን እና የተግባር ልምዶችን በጥልቀት በመወያየት ለተቋማችን የተሻለ የአሰራር ባህል ለመገንባት እንጠቀማለን ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ውጤታማ የግዢና ንብረት አስተዳደር ማለት ህግን ማክበር ብቻ ሳይሆን የህዝብ ሀብት በኃላፊነት መጠቀም ብክነትን መከላከል፣ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና ለተቋሙ ዘላቂ ተቋማዊ አቅም መፍጠር ማለት ጭምር መሆኑን አብራርተው ሁሉም ሰራተኛ የሥራ ዘርፍ ሕጋዊነትን፣ተጠያቂነትን እና ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በጽናት እንድናሰፈን ይጠበቃል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያቤቱ የስነምግባር መከታተያ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጸሐይ ሽፈራው ባስተላለፉት መልዕክት የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት የመንግስት ተቋማት ተልዕኳቸውን በብቃት፣በታማኝነትና ተጠያቂነት እንዲፈጽሙ ከሚያስችሉ ዋና ዋና የአስተዳደር ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የግዢ ሂደቶች በሕግ መሰረት መመራታቸውን፣የመንግስት ሀብት በአግባቡ መጠበቁንና መተዳደሩ እንዲሁም የህዝብ ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ ለማዋል እንደዚህ ዓይነት ስልጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናውን ከግዢ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመጡ ባለሙያዎች ሰጥተዋል፡፡

