በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስተባባሪነት በትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ድርጅቶች ልምድ ልውውጥ ተደረገ።

ምናልባት የአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች እና የሚያጠኑ ሰዎች ምስል
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በስሩ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውጤታማ ስራዎችን ሰርተው ሀገርንና ማህበረሰቡን በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችሉ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። ይህንኑ ተከትሎ በትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩት የሳንፎርድና ቀለም ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች ደብረ ብርኃን ከተማ ከሚገኘውና በምዝገባ ሂደት ላይ በሚገኘው የሀይሌ ማናስ አዳሪ ትምህርት ቤት ተገኝተው የልምድ ልውውጥ አድርገዋል። የልምድ ልውውጡ በትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ የዘለቄታ በጎ አድራጎት (charity endowment) ድርጅቶች ውጤታማና ብቁ የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆችን ለማፍራት ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥራትንና ውጤታማነትን መሠረት ያደረገ ትምህርት በመስጠት አሰራራቸውን እንዲያዘምኑና የተቋቋሙበት አላማ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን እገዛ የሚያደርግ ነው።ሀይሌ ማናስ አካዳሚ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ የአዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን በስሩ ከ260 በላይ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ተማሪዎችን ይዞ በማስተማር ላይ የሚገኝ የትምህርት ተቋም ነው። አካዳሚው ዘመናዊ እና እጅግ የተሟላ መሠረተ ልማት የያዘ ሲሆን የሀገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ ተከትሎ ውጤታማ ተማሪዎችን እያፈራም ይገኛል። በቅርቡም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ቀርቦ የምዝገባ ሂደቱን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን አካዳሚው ውጤታማነቱን በማስቀጠል ህብረተሰቡን በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ ለማድረግ በጥረት ላይ ይገኛል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አካዳሚው እየተከተለው ያለው የትምህርት አሰጣጥ ለሌሎች መሠል ተቋማት ከልምድ አንጻር ያለውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ቀለም እና ሳንፎርድ ያሉ ሀገር በቀል የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ አስችሏል።