የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በደቡብ ወሎ ዞን 037 ቀበሌ ለአራት መቶ ተማሪዎች የትምህት ቁሳቁስ ድጋፍ፣የችግኝ ተከላ መርሃግብር እና በቀጣይ ለሚያስገነባቸው የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የማኖር መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡ በመርሃግብሩ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ፣ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ፣አቶ ተስፋ ዳኘው የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ጽ/ቤት ሃላፊ ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በመክፈቻ ንግግራቸው ባስተላለፉት መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ የተጀመረ ብሔራዊ ንቅናቄ መሆኑን በመግለጽ በጎ ፈቃድ ሥራ ገንዘብ ሳይሆን ጊዜያችን፣ ጉልበታችን፣ እውቀታችን እና ፍቅራችን የምናጋራበት እና የምንሰራው ትንሽ ስራ በሌላ ሰው ሕይወት ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ተግባር በመሆኑ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከዚህ አንጻር በጎ ፈቃድ ሥራ የዛሬን ችግር ብቻ የሚፈታ ሳይሆን የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት ባህልን በማጠናከር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሠረት የሚጥል ተግባር በመሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጉልህ ተሳተፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ።

አያይዘውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገራችን የልማት፣ የሰላም፣ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የዜጎች ተሳትፎ ማጎልበት ውስጥ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ሁሉ በጎ ፈቃደኝነትም ከእነዚህ እሴቶች የሚመነጭ ተግባራዊ መገለጫ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በማለት ለዚህ ፕሮግራም መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የዞኑ የስራ ሃላፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋ ዳኘው በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት በክረምት የበጎ ፍቃድ ስራ ሶስት ግቦችን በማስቀመጥ አቅዶ እየሰራ መሆኑን በመግለጽ በዘንድሮ በጀት ዓመት ብቻ 1276 የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ ለማከናወን አቅደው ከጅምሩ 326 ቤቶችን ማስገንባት መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሃላፊው እንዳሉት በበጎ ፍቃድ ስራ የውስጥ አቅም፣ የመረዳዳት ባህል እያደገ እና የማህበረሰቡም ችግር እየተቀረፉ መምጣቱን ጠቅሰው ባለስልጣን መስሪያቤቱም ይህንን ተግባር ለማጠናከር በመገኘቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡