የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ከተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብና የአልባሳት እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከተለያዩ የምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች ተፈናቅለው በነቀምቴ ከተማ ለሚገኙ ግምታቸው ከ1.1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የምግብና የአልባሳት እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስተባባሪነት ከፍሪድ ሃሎውስ ፋውንዴሽን ሰራተኞች መዋጮ፣ ከአጋር ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ፣ ከአሜን በጎ አድረጎት ድርጅት እና ሌሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የተዘጋጀ ሲሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በምስራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ ተገኝተው ለነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ምስጋኑ ቱሉ እና በከተማው ለሚገኘው የድጋፍ አሰባሳቢ ቢሮ (ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ) ተወካይ መስጋኑ ወጋ አስረክበዋል፡፡

በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በነቀምቴ ከተማ በመጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ሆነው የተደረገ ድጋፍ መሆኑን ጠቁመው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወገኖቻችን በሚደረግ የድጋፍ እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ለዚሁ ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ ምስጋኑ ቱሉ በተደረገው ድጋፍ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው ድጋፉን ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር የምግብና የአልባሳት እንዲሁም የንጽህና ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡:
በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በየወሩ የሚያካሄደው ተቋማዊ የንባብ ቀን ለ8ኛ ጊዜ ተዘጋጅቷል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች ተሳታፊ የሆኑበት ተቋማዊ የንባብ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የተቋማችን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለጹት ይህ በተቋም ደረጃ የተጀመረው የማንበብ ባህል በጣም ጠቃሚ እና አስተማሪ መሆኑን ገልጸው ከዚህ የበለጠ የንባብ ቀን አባላት በስራ እና በስነምግባር አራያ ሆነው ለሌሎች ተቋማት የምናስተላልፈው ሞዴል ተግባር እንዲሆን መስራት አለብን ብለዋል ፡፡

አያይዘውም 17ተኛው የፌደራል የመንግሥት መ/ቤቶች የሴቶች የቫሊቦል ውድድር ላይ ተቋማችን ሰርተፍኬት ተሸላሚ መሆኑን ገልጸው በጨዋታ ብቃትዋና በስፖርታዊ ጨዋነትዋ የተቋማችን የበጎ ፈቃድ ዴስክ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሽልማት መርሻ የወርቅ ሜዳለያ ተሸላሚ በመሆናቸው ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የንባብ ቀን ዓላማ የሰራተኞችን የማንበብ ባህል እንዲጎለብት ለማድረግ ፣ ከተለያዩ የተቋሙ ሰራተኞች የህይወት ልምድ የሚቀሰምበት ብሎም እርስ በእርስ የሚያቀራርብ መድረክ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከቱ ጌዘር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለተቋሙ ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡

ስልጠናው ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ዓይነ ስውራን ተገልጋዮች መደረግ ስላለበት ድጋፍና ዓይነስውራንን በሚመለከት ያለውን ግንዛቤ ማሰዳግ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ በስልጠናው ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱን ጨምሮ የቱ ጌዘር ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ በላይ እንዲሁም የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡ ስልጠናውን ያስጀመሩት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ቱ ጌዘር ኢትዮጵያ በአይነስውራን ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለድርጅት መሆኑን በአካል በድርጅቱ ተገኝተው መመልከታቸውን አስታውሰው ከባለስልጣኑ ጋር እየሰራ ባለው ስራ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የቱጌዘር ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ብርኃኑ በላይ በበኩላቸው ድርጅታቸው ቱ ጌዘር ኢትዮጵያ ዓይነ ስውራንን መሰረት ያደረጉ 5 ፕሮጀክቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ዓይነስውራን ከዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ጋር ያላቸውን ተግባቦት ለማሳደግ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስልጠናዎችን በመስጠት ለCOC ብቁ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በዚህም በተለያዩ ምክንያቶች ክትምህርት ገበታቸው የተስተጓጎሉ ዓይነ ስውራንን ወደትምህርት ገበታቸው መመለስ መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም በ10 ዓመት ውስጥ ከ36 ሺህ በላይ ዓይነስውራንን በቀጥታ ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎችን መስራታቸውን ተናግረዋል፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቻይናውያን ዜጎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተደረገ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር መካካል የበጎ ፈቃደኝነትን ባሕልና እንቅስቃሴን ማበረታታት፤የበጎ ፈቃደኝነትን በተመለከተ የስርጸት ስራ የመስራት ተግባር አንዱ ነው፡፡ ይህን ተግባር እውን ለማድረግ ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር ህግንና አሰራርን መሰረት በማድረግ በትብብር እየተሰራ ይገኛል፡፡
ይህንኑ መሰረት በማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ትብብር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሉላ ሚሊዮን መሰረቱን በቻይና ሀገር ካደረገው ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት (China Foundation for Rural Development) አለም ዓቀፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡:

ድርጅቱ ከ5 ዓመት በፊት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ስር ተመዝግቦ በትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና በድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች ላይ በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የቻይና ኩባንያዎች ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙ ቻይናውያን ዜጎችን በተለያዩ ሙያዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ማሰማራት ይፈልጋል፡፡
ይህንኑ መሰረት በማድረግ ከ100 በላይ በኢትዮጵያ ባሉ የቻይና ኩባንያዎች ውስጥ የሚሰሩ ቻይናውያን ዜጎች የተለያዩ ሙያዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን መስጠት እንዲችሉ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን ባለስልጣኑ ባዘጋጀው የ voluntarism management information system (VMIS) ተመዝግበው በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ ሙያዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ መስጠት እንዲችሉ እንደሚደረግ በውይይቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በጫካ ፕሮጀክት ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ለሚፈልጉ በጎ ፈቃደኞች በባለስልጣኑ በኩል ተሳትፎ የሚያደርጉበት ሁኔታ የተመቻቸ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደተግባር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የቻይናውያን ዜጎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ የእውቀትና የባህል ሽግግር በማድረግ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የያዘውን በማህበረሰቡ ውስጥ በጎ ፈቃደኝነትንና በጎ አድራጊነትን ባህል የማድረግ እንቅስቃሴ በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነም በውይይቱ ተገልጿል፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጉብኝት አደረጉ፡፡
በሁለቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህ የተመራ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ልዑካን ቡድን በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረገበት ወቅት የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ አቀባበል አድርገዋል፡፡ የተቀናጀ አሳታፊ እና ዘላቂ የልማት ፕሮግራሞችን በማከናወን ለድህነት ተጋላጭና ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማብቃትና ከድህነት ማውጣት የሚል ተልዕኮ አንግቦ ከ30 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ አስኮ አካባቢ የተጀመረው የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ስራ በአሁን ጊዜ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከ160 በላይ ቀበሌዎችንና ወረዳዎችን በማካለል የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በተግባር እየተወጣ የሚገኝ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ስር ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡
የዚህን ድርጅት የስራ እንቅስቃሴ በሚመለከት ገለጻ ያደረጉት የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ድርጅታቸው በትምህርትና ስልጠና፣ በጤና አገልግሎት፣ የመንግስትና የግሉ ዘርፍን አጋርነት በማጠናከር እንዲሁም በኢኮኖሚ አቅም ግንባታ በርካታ ህጻናትን፣ አረጋውያንን፣ ወጣቶችን እንዲሁም ለጎዳና ህይወት የተጋለጡ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

“ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን” በሚል ፕሮግራም ድርጅቱ በ6 ክፍለ ከተሞች በጎ አድራጊ አትዮጵውያንን በማስተባበር አረጋውያንንና ህጻናትን ቤት ለቤት ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በጎዳና ላይ ለወደቁ እናቶች የኢኮኖሚ አቅም ግንባታ ስራዎችን በመስራት ላይም ይገኛል፡
የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው የተመለከቱት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ኢትዮጵውያን ከተባበሩ የኢትዮጵያውያን ችግር ከኢትዮጵያውያን በታች እንደሆነ ማሳያ የሚሆን ትልቅ ስራ ድርጅቱ እየሰራ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን ድርጅቱ ግልጽና ተዓማኒነት ያለው ስራ በመስራቱ በበርካታ ኢትዮጵውያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው ስራ መስራት እንደቻለ ገልጸዋል፡፡
በጉብኝቱ የኢትዮጵያውያንን የመተባበር ውጤት በጉልህ እንደተመለከቱ የጠቆሙት የስራ ኃላፊዎቹ በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የታየው ተቋማዊ አቅም፣ የዲጂታላዊ መረጃ አያያዝና እና አሰራርን የተከተለ የተቋም ግንባታ ዘርፉ ውጤታማ ስራ መስራት እንዲችል ትልቅ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ድርጅቱ እየሰራ ያለው ስራ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
ዳግም ባልተመዘገቡ እና ሪፖርት ባላቀረቡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጥ ቦርዱ ገለጸ፡፡
ዳግም ምዝገባ ባላደረጉ 1558 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችናህልውናቸውን ባላረጋገጡ 296 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ቦርድ አስታውቋል፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር በመተባበር በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት ዳግም ምዝገባ ባላደረጉ እና የ2013 በጀት አመት ሪፖርት ያላቀረቡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በተመለከተ ውይይት ለማድረግ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ በመድረኩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢና የፕላንና ልማት ሚንስቴር ሚንስትር ደኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃና ወልደገብርኤል እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል፡፡ አዋጅ 1113/2011 መሰረት በቀድሞው አዋጅ 621/2001 የተመዘገቡ ድርጅቶች በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ቀርበው መመዝገብ እንዳለባቸው የሚደነግግ ሲሆን በዚሁ መሰረት 1558 የሚሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዳግም ባለመመዝገባቸው እና 296 ድርጅቶች ህልውናቸውን ባለማረጋገጣቸው ለባለስልጣኑ ቦርድ ለውሳኔ ማቅረቡን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ገልጿል፡፡

በዚህም መነሻነት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት አባላት ጋር ውይይት እንዲደረግ አቅጣጫ ማስቀመጡ በመድረኩ ተገልጿል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት ሪፖርት በማቅረብ ህልውናቸውን ባላረጋገጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የመጨረሻ ውሳኔ ሚያዚያ 20/ 2016 ዓ.ም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ቦርድ ውሳኔ እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን በሚቀጥሉት 30 ቀናት ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቀርበው ሪፖርት እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከአንድ አመት በላይ ዳግም ያልተመዘገቡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዳግም እንዲመዘገቡ በተለያየ መልኩ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርግም መመዝገብ ያለመቻላቸውን ተገልጾ አሁን ቦርዱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሪፖርት ማያደርጉ ከሆነ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመጨረሻ የተባለውን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም በመድረኩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቦርድ ጽህፈት ቤት መመሪያ ቁጥር 970/2015 መሰረት የተቋቋመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚቀርቡ የይግባኝ ጥያቄዎችን በመመሪያው መሰረት በመቀበል እልባት የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች የሴቶች ቀንን /March 8/ አከበሩ፡፡
በዓለማቀፍ ደረጃ 113ኛ ግዜ በሃገራችን ለ48ኛ ጊዜ ‹‹ሴቶችን እናብቃ፤ ልማት እና ሰላምን እናረጋግጥ›› በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ጸሐይ ሽፈራው እንደተናገሩት በየዓመቱ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የንቅናቄ ተግባራት የሚከበር መሆኑን ገልጸው የንቅናቄው ዋና ዓላማ በዓለም ላይ ያሉ መንግስታት የሴቶች ጉዳይ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጉዳይ እንደሆነ አምነው በመቀበል በሴቶች ዙሪያ ፖሊሲዎቻቸውን ህጎቻቸውንና አሰራሮቻቸውን በመፈተሸ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ መድልዎችን እንዲያስወግዱና የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ብሎም ጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ለማነሳሳት፣ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዬች እንዲበቁ እና በሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት ጉዳዬች ዙሪያ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ እና ሌሎች ዓላማዎችን መሰረት ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አቶ ፍቃዱ ወ/ሰንበት የተቋሙ የጽ/ቤት ሃላፊ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት የዓለማቀፍ የሴቶች ቀን ሲከበር ለማክበር ብቻ ሳይሆን ሴቶችን በሁለንተናዊ ጉዳዬች ላይ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ በማድረግ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በመንግስት የስራ ሃላፊነቶች ላይ እና በተለያዩ ጉዳዬች ዙሪያ የሴቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት መንግስት እየሰራ መሆኑን አንስተው በተቋማችንም ሴቶችን ከማቃት አንጻር የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ የሃገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የሆነው የቤተሰብ መምሪያ ማህበር በመድረኩ ላይ ስለማህጸን በር ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የሰሩ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ለባለስልጣን መስሪያቤቱ ሴት ሰራተኞች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ በስጦታ አበርክተዋል፡፡
10ኛው የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የክልልና የፌደራል ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባኤ ተጠናቋል፡፡
በጉባኤው በርካታ ርዕሰ ጉዳዬች የተዳሰሱ ሲሆን በተለይም ጉባኤው ከተጀመረ ጀምሮ የተሻሻሉ እና የተገኙ ውጤቶች ፣የሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዴስክ ሃላፊዎች የተወያዩባቸው ርዕሰ ጉዳዬች ፣የራስ በራስ የማስተዳደርና ልምምድ እና አተገባበር በኢትዬጵያ ፣የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃና ኢነርጂ ላይ ከሚሰሩ የሲማድ ጋር የጀመራቸውን መልካም ስራዎችን በተመለከተ እና CSSP2 በዘርፉ እያከናወናቸው ስላሉ ጉዳዬች ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡በማጠቃለያውም የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ጉባኤው ከግዜ ወደ ግዜ መሻሻሎች እያሳየ መምጣቱን አንስተው ይህንን ጉባኤ ለማጠናከር ሁሉም ክልሎች እና ሴክተር መስሪያቤቶች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየዘርፍ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መደገፍ፣መከታተልና፣መቆጣጠር እንዲሁም በጉባኤ የተሰጡ አቅጣጫዎችን መፈጸም እና በቀጣይ መገምገም የዚህ ጉባኤ ቁልፍ አቅጣጫ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በመጨረሻም ይህ ጉባኤ ተጀምሮ እዚህ እስኪደርስ ድረስ በገንዘብና በቴክኒክ ድጋፍ ላደረጉት CSSP2 ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
10ኛው የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የክልልና የፌደራል ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባኤ በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የቤኒሻንጉል ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት የሀገራችን እና የክልላችን መንግሥት በየዘርፉ የነደፏቸውን ዕቅዶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በማጠናቀቅ ባንድ በኩል የህዝብን ተጠቃሚነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሀገራችን የብልፅግና ጉዞ ስኬታማነት ተደማሪ አቅም ለመፍጠር የጋራ ርብርብ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ በዚህ የጋራ ጥረትና ርብርብ ውስጥ ደግሞ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እገዛና ድጋፍ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ ምክንያት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ዘርፉ የሚመራበትን አዋጅ በማፅደቅ ተግባራዊ ማድረጋቸውን እና በእስካሁኑ ሂደት የተመዘገቡ ለውጦችም አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ የተጀመሩ የጋራ ጥረትና ርብርብ ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ በመግለጽ በዚህ ረገድ እንደመንግሥት በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር የጀመርነውን የጋራ ጥረት የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቅብናል ሲሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው ሁሉም የፌዴራል ሴክተር መ/ቤቶች እና የክልል መንግስታት በዘርፉ በተጨባጭ የህዝብን ችግር የሚቀርፍ ሥራ እየሰሩ ስለመሆኑ ቋሚ የግንኙነት መድረክ በመፍጠር ጭምር ተገቢውን የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ድጋፍ ስራ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ በዚህ ጉባኤ ትኩረት ሰጥቶ ሊመከርበት የሚገባው ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አገራችን የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ተከታታይ ፈተናዎችን በመቋቋም ዕዳዎችን ወደ ምንዳ በመቀየር በቁርጠኝነት ወደፊት መጓዝን የሚጠይቅ ሲሆን ለተግባራዊነቱ በጋራ መቆም ወሳኝ ነው ከዚህ አንፃር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ እና ከኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር በጋራ መስራት በሚያስችለው ጉዳዬች ዙሪያ የሶስትዬሽ ስምምነት ተፈራረሙ።
በስምምነቱ ላይ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። ዛሬ በተደረገው ስምምነት ላይ የሶስቱ ተቋማት የስራ ሃላፊዎችም ስለ ስምምነቱ አስፈላጊነት ብሎም በቀጣይ በጋራ ስለሚሰሯቸው ጉዳዮች ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል። የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ርዕሰ አካዳሚ ዛዲግ አብርሃ፤ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ለማሳለጥ ብቁ የሆነ አመራርን ማፍራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። አካዳሚው በተለያዩ የስራ መስኮች ብቁ እና ጠንካራ አመራሮችን ለማፍራት ከተለያዩ አካላቶች እና ተቋማቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የስምምነቱ ዋና ዓላማ በሀገሪቱ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮችን አቅም ማጎልበት ብሎም በዘርፉ አርአያ እንዲሆኑ ማብቃት መሆኑን አንስተዋል። ርዕሰ-አካዳሚው ዛዲግ አክለውም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ብሎም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጠንካራ አመራር ማፍራት ላይ በጋራ የምንሰራቸውን ስራዎች አጠናክረን መሄድ ይጠበቅብናል ብለዋል። በሀገሪቱ ጠንካራ እና ብቁ የሆነ አመራርን ማፍራት ስንችል የኢትዮጵያን ብልጽግና በፍጥነት ማረጋገጥ እንችላለን ነው ያሉት ።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት የሪፎርም ማሻሻያዎች ካደረገባቸው የስራ ዘርፎች አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ እንደሆነ ጠቁመዋል። በተደረገው የሪፎርም ማሻሻያም ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምቹ የስራ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል። ይሁን እንጂ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሀገሪቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ቢያከናውኑም ካላቸው አቅም አንጻር ያበረከቱት ሚና በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም ድርጅቶቹ ያላቸውን አቅም በሚገባ ተጠቅመው አለመስራት ፣ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ተቋም አለመገንባት መሆኑን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ለተቋቋሙለት ዓላማ አበክሮ ያለመስራትና የፋይናንስ ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችላቸውን አቅም አለመፍጠር እንደሆነ አብራርተዋል። እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት ብቁ የሆኑ አመራሮች በዘርፉ ማፍራት ተገቢ መሆኑን አንስተው ይህንንም ለማድረግ የሚያግዝ ፊርማ ዛሬ ተፈራርመናል ብለዋል። የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አህመድ ሁሴን በበኩላቸው በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥና የሀገርና የህዝብ ችግሮችን ለመፍታት ተቋማቶች በጋራ ተቀናጅተን መስራት የሚጠይቅበት ወቅት ነው ብለዋል። በመሆኑም የስምምነት ፊርማው እንደ ሀገር ተጨባጭ እድገትን ለማምጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ እውን ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።











