የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከተለያዩ የምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች ተፈናቅለው በነቀምቴ ከተማ ለሚገኙ ግምታቸው ከ1.1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የምግብና የአልባሳት እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስተባባሪነት ከፍሪድ ሃሎውስ ፋውንዴሽን ሰራተኞች መዋጮ፣ ከአጋር ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ፣ ከአሜን በጎ አድረጎት ድርጅት እና ሌሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የተዘጋጀ ሲሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በምስራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ ተገኝተው ለነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ምስጋኑ ቱሉ እና በከተማው ለሚገኘው የድጋፍ አሰባሳቢ ቢሮ (ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ) ተወካይ መስጋኑ ወጋ አስረክበዋል፡፡
May be an image of 2 people and text
በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በነቀምቴ ከተማ በመጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ሆነው የተደረገ ድጋፍ መሆኑን ጠቁመው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወገኖቻችን በሚደረግ የድጋፍ እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ለዚሁ ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ ምስጋኑ ቱሉ በተደረገው ድጋፍ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው ድጋፉን ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር የምግብና የአልባሳት እንዲሁም የንጽህና ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡: