የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር መካካል የበጎ ፈቃደኝነትን ባሕልና እንቅስቃሴን ማበረታታት፤የበጎ ፈቃደኝነትን በተመለከተ የስርጸት ስራ የመስራት ተግባር አንዱ ነው፡፡ ይህን ተግባር እውን ለማድረግ ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር ህግንና አሰራርን መሰረት በማድረግ በትብብር እየተሰራ ይገኛል፡፡
ይህንኑ መሰረት በማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ትብብር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሉላ ሚሊዮን መሰረቱን በቻይና ሀገር ካደረገው ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት (China Foundation for Rural Development) አለም ዓቀፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡:
May be an image of 4 people, people studying and text
ድርጅቱ ከ5 ዓመት በፊት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ስር ተመዝግቦ በትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና በድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች ላይ በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የቻይና ኩባንያዎች ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙ ቻይናውያን ዜጎችን በተለያዩ ሙያዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ማሰማራት ይፈልጋል፡፡
ይህንኑ መሰረት በማድረግ ከ100 በላይ በኢትዮጵያ ባሉ የቻይና ኩባንያዎች ውስጥ የሚሰሩ ቻይናውያን ዜጎች የተለያዩ ሙያዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን መስጠት እንዲችሉ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን ባለስልጣኑ ባዘጋጀው የ voluntarism management information system (VMIS) ተመዝግበው በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ ሙያዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ መስጠት እንዲችሉ እንደሚደረግ በውይይቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በጫካ ፕሮጀክት ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ለሚፈልጉ በጎ ፈቃደኞች በባለስልጣኑ በኩል ተሳትፎ የሚያደርጉበት ሁኔታ የተመቻቸ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደተግባር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የቻይናውያን ዜጎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ የእውቀትና የባህል ሽግግር በማድረግ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የያዘውን በማህበረሰቡ ውስጥ በጎ ፈቃደኝነትንና በጎ አድራጊነትን ባህል የማድረግ እንቅስቃሴ በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነም በውይይቱ ተገልጿል፡