በሁለቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህ የተመራ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ልዑካን ቡድን በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረገበት ወቅት የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ አቀባበል አድርገዋል፡፡ የተቀናጀ አሳታፊ እና ዘላቂ የልማት ፕሮግራሞችን በማከናወን ለድህነት ተጋላጭና ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማብቃትና ከድህነት ማውጣት የሚል ተልዕኮ አንግቦ ከ30 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ አስኮ አካባቢ የተጀመረው የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ስራ በአሁን ጊዜ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከ160 በላይ ቀበሌዎችንና ወረዳዎችን በማካለል የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በተግባር እየተወጣ የሚገኝ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ስር ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡
የዚህን ድርጅት የስራ እንቅስቃሴ በሚመለከት ገለጻ ያደረጉት የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ድርጅታቸው በትምህርትና ስልጠና፣ በጤና አገልግሎት፣ የመንግስትና የግሉ ዘርፍን አጋርነት በማጠናከር እንዲሁም በኢኮኖሚ አቅም ግንባታ በርካታ ህጻናትን፣ አረጋውያንን፣ ወጣቶችን እንዲሁም ለጎዳና ህይወት የተጋለጡ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

May be an image of 13 people and text

“ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን” በሚል ፕሮግራም ድርጅቱ በ6 ክፍለ ከተሞች በጎ አድራጊ አትዮጵውያንን በማስተባበር አረጋውያንንና ህጻናትን ቤት ለቤት ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በጎዳና ላይ ለወደቁ እናቶች የኢኮኖሚ አቅም ግንባታ ስራዎችን በመስራት ላይም ይገኛል፡
የድርጅቱን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው የተመለከቱት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ኢትዮጵውያን ከተባበሩ የኢትዮጵያውያን ችግር ከኢትዮጵያውያን በታች እንደሆነ ማሳያ የሚሆን ትልቅ ስራ ድርጅቱ እየሰራ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን ድርጅቱ ግልጽና ተዓማኒነት ያለው ስራ በመስራቱ በበርካታ ኢትዮጵውያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው ስራ መስራት እንደቻለ ገልጸዋል፡፡
በጉብኝቱ የኢትዮጵያውያንን የመተባበር ውጤት በጉልህ እንደተመለከቱ የጠቆሙት የስራ ኃላፊዎቹ በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የታየው ተቋማዊ አቅም፣ የዲጂታላዊ መረጃ አያያዝና እና አሰራርን የተከተለ የተቋም ግንባታ ዘርፉ ውጤታማ ስራ መስራት እንዲችል ትልቅ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ድርጅቱ እየሰራ ያለው ስራ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡