የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን volunteer services overseas (VSO) ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃድና የበጎ ፈቃድ መረጃ አስተዳደር ስርዓት (VMIS) ዙሪያ ስልጠና ሰጠ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን volunteer services overseas (VSO) ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃድና የበጎ ፈቃድ መረጃ አስተዳደር ስርዓት (VMIS) ዙሪያ ስልጠና ሰጠ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከ VSO ጋር በመተባበር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአምስቱ ካንፓሶች ለሚገኙ ተማሪዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽንሰ ሃሳብና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሙያዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እገዛ የሚያደርገውን የበጎ ፈቃድ መረጃ አስተዳደር ስርዓት (VMIS) በሚመለከት ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህ እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ህክምና አገልግሎት ምክትል ኮርፖሬት ተወካዮች እና በአምስቱ ካንፓሶች የሚማሩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው የትምህርትና ህክምና አገልግሎት ምክትል ኮርፖሬት ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ሙሉቀን ብርሃኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ትኩረት ማግኘት በመቻሉ ተማሪዎች ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያላቸውን ተነሳሽነት የሚያዳብር መሆኑን ጠቁመው መሰል ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች የተማሪዎችን አቅም በማጎልበት ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎች በተማሪዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ተወካዩ ከስልጠናው በኋላ ተማሪዎች ቀደም ሲል ይሰጡት ከነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሻለ ውጤታማ ስራ መስራት እንዲችሉ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ሀገራት ወደተሻለ ስልጣኔ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንስተው የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን የተላበሰ ማህበረሰብ ሀገርን በመገንባት ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የተላበሰ ማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ችግር እንደማይገጥመው ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ አብሮነትን፣ ህብረ ብሄራዊነትን ማዕከል ያደረገ፣ የሚተሳሰብ፣ እርስ በርስ የሚረዳዳ እና ሀገራዊ ስብራቶችን ለመጠገን በጎ ፈቃድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው የጠቆሙ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎች የበጎ ፈቃደኞች መሰባሰቢያ እና ማዕከል እንዲሆኑና ሀገር ከበጎ ፈቃደኞች ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ እንድትሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዳማ፣ ወራቤ፣ ወልቂጤና አሁን ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ የጠቆሙ ሲሆን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ይኸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የበጎ ፈቃደኞች ማዕከል እንዲሆን እንፈልጋለን ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ክበቦችን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በከተማው ውስጥ በሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን በመስጠትና በዩኒቨርሲቲው ውስጥም ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን በመከወን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡ እሴት እንዲሆን የበኩላችሁን እንድትወጡ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምንነትንና ጽንሰ ሀሳብን በሚመለከት ስልጠናውን የሰጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ትብብር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሉላ ሚሊዮን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር መካከል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማህበረሰቡ ውስጥ ባህል እንዲሆን ማስቻል መሆኑን ጠቁመው ስልጠናው በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሙያቸው እና በተማሩበት የትምህርት መስክ የሙያ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግላቸው አንስተዋል፡፡
ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን የተሰጠውን ስልጠና ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር ያዘጋጀው ከባህር ማዶ በጎፈቃድ አገልግሎት ድርጅት ወይም በእንግሊዘኛው አጠራር volunteer services overseas (VSO) በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ድርጅት ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ጌታያውቃል አብርሃም ድርጅቱ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ በበጎ ፈቃድ፣ በተቀናጀ ልማት፣ በትምህርትና አቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸው ከስልጠናው በኋላም በዩኒቨርሲቲው ለሚገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ክበባት ትስስርe በመፍጠር ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል፡፡ በስልጠናው ላይ volunteer services overseas (VSO) በኢትዮጵያ ውስጥ እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን በጎ ፈቃድን በማህበረሰቡ ውስጥ የማስረጽና ባህል የማድረግ ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት መሰል ስልጠናዎችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የበጎ ፈቃድ ክበባትን የማጠናከርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡


ባለስልጣን መስሪያቤቱ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአራቱ ድርጅቶች እግድ መነሳት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጿል፡፡

ባለስልጣን መስሪያቤቱ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአራቱ ድርጅቶች እግድ መነሳት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጿል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ምክር ቤቱ በተለያዩ ጊዚያት ባለስልጣን መስሪያቤቱ ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን በሂደቱ ከመጀመሪያ ጀምሮ የሄደበት ርቀት ሙያዊ፣ተግባርና ሃላፊነቱን የጠበቀ እና ችግሩን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ መደላድል የፈጠረ ነበር ተብሏል።
ምክርቤቱ ችግሮችን ለመፍታት የሄደበት መንገድ በጣም አስተማሪ መሆኑን አንስተው በዘርፉ የተጀመረውን ሪፎም ለማስቀጠል እና ለማጽናት የራስ በራስ ቁጥጥርን በማጠናከር ከዚህ የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅበት በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።
ባለስልጣን መስሪያቤቱም በአራቱ ድርጅቶች እግድ መነሳት ላይ ምክርቤቱ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርቧል፡፡

የምክርቤቱ ስራ ሰአስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት በድርጅቶቹ መታገድ ከፍተኛ ጫና ውስጥ መግባታቸውን አንስተው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጉዳዩን በሰከነ አእምሮ እና በመናበብ መስራታቸውን አንስተው ባለስልጣን መስሪያቤቱም ለድርጅቶቹ እግዱን በማንሳቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመነጋገር የማይፈታ ችግር የለም ያሉት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ ለሃገር አድገትና ለማህበረሰቡ የጋራ ተጠቃሚነት በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ የባለስልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች ከምክርቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡


የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ያላቸውን የስራ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ለማድረግ የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄደ።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ያላቸውን የስራ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ለማድረግ የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄደ።

ውይይቱ የካቲት 22 ቀን 2017 በቢሾፍቱ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮችና አና ስራ አስፈጻሚ አባላት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ አባላትና ሴክሬታሪያት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በጋራ በሚሰሩ ጉዳዬች ላይ የመከሩ ሲሆን በዚህ መድረክም በሁለቱም አካላት በተውጣጡ ኮሚቴዎች አማካኝነት የተዘጋጀ ረቂቅ ስትራቴጂያዊ የትብብር ማዕቀፍ ሰነድ ቀርቦ ውይይት በማድረግ ግብዓት የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል፡፡ ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የመመዝገብ፣ የመቆጣጠርና ድጋፍ የማድረግ ተልዕኮው መሰረት በማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም ዘርፉን የሚወክል ተቋም ከመሆኑ አንጻር ከምስረታው ጀምሮ አገራዊና ዘርፉን የተመለከቱ ጉዳዬችን በትብብር እና አጋርነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ሁለቱ ተቋማት ትብብሩን ስትራቴጂያዊ ማድረግ ወጥነት ባለው መልኩና በዘላቂነት ለማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት የትብብር ማዕቀፉ ሊዘጋጅ እንደቻለ በመድረኩ ተገልጿል።
ማዕቀፉ ተቋማቱ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጠና በአገራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ጠንካራ የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፍ ለመገንባት ያላቸውን የጋራ አላማ ውጤታማ በማድረግ ረገድ አጋዥ እንደሆነ በመግለጽ በመድረኩ የተሰጡ ግብአቶች ተካተው በአጭር ጊዜ እንዲቀርብና በተቋማቱ በጋራ ጸድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ በተከሰቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ፣የእግድ ላይ በሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የUSAID ጊዜያዊ የሥራ ማቆም ውሳኔ በሴክተሩ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ በተመለከተ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የመፍትሄ ሃሳቦች ተነስተው አቅጣጫ በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል፡፡


ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ሰብዓዊ ድጋፍ ኮሚሽን እና ቲርፈንድ በድሬደዋ እና በምስራቅ ሃረርጌ ያከናወኗቸውን የልማት ስራዎች ተመልክተዋል፡፡

ዶ/ር ተፈራ ታሎሬ የኢትዮጰያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ሰብዓዊ ድጋፍና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ድርጅቱ በኢትዮጵያዊያን አቆጣጠር ከሃምሳ አንድ ዓመት በፊት በ1966 ዓ.ም በወሎ በተከሰተው ድርቅና ርሃብ ምክንያት እርዳታ በማድረግ ስራ መጀመሩን ገልጸው በዋናነት በትምህርት፣በሰላም ግንባታ፣በሰብዓዊ ድጋፍ እና ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በሃገሪቱ አንድ መቶ አርባ (140) ፕሮጀክቶች ስራ ላይ መሆናቸውን ገለጸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሪፖርት በተጨማሪ በአካል የድርጅቱን ስራ ለመመልከት በመገኘቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የቲር ፈንድ የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ Simba Gorden Nyamarezi በበኩላቸው የተሻለ ልማትና ውጤት ማምጣት የሚቻለው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት ሲቻል መሆኑን ጠቅሰው ከባለስልጣን መስሪያቤቱ ጋር የጀመርነውን ትስስር አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በድሬደዋ ፣ምዕራብ ሃረርጌ እና በጂግጂጋ ድርጅቱ የሰራቸውን ስራዎች በሪፖርት የቀረበ ሲሆን በጉብኝቱም በርካታ ሰው ተኮር ስራዎች መሰራታቸውን መመልከት ተችሏል፡፡
የድሬደዋ ከተማ የቃለህይወት የልጆችና ወጣቶች የልማት ፕሮጀክት በአስር ዓመታት ቆይታው በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን የጠቀሱት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ታደሰ ቢረዳ ዝቅተኛ የኑሮ ጀረጃ ላይ ለሚገኙ ዘጠኝ መቶ አስራ ስምት ልጆች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ድርጅቱ ከኬጂ ጀምሮ አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲ የሚያስተምራቸው ልጆች መኖራቸውን አብራርተው ከዚህ በተጨማሪ ለልጆቹ የህክምና ፣ የምግብ ቁሳቁስ ፣ የትምህርት ቤት ግብዓቶችን በሟሟላት እና ለወላጆች በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲችሉ ለስልሳ ወላጆች የተለያዩ የሙያ ስልጠና መስጠቱን አብራርተዋል፡፡
በባለፉት አስር ዓመታት አንድ መቶ ሃያ ስድስት ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን በመግለጽ ፕሮጀክቱ የልጆች ስነምግባር ፣አካላዊ እና ማህበራዊ ዕድገት ፣በትምህርት እና አስተዳደራዊ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ህጻናቱ በሰጡት አስተያየትም ድርጅቱ እርዳታ ባያደርግላቸው የዕለት ጉርስ ፍለጋ ከትምህርታቸው ሊስተጓጎሉ ይችሉ እደነበር ገልጸው ቃለ ህይወት የእርዳታ ኮሚሽንን ስለሚያደርግላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ ሐረር ሚደጋ ቶላ ላይ ሃምሳ አምስት ሺህ (55000) የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርግ እና በሶስት ዓመት የሚጠናቀቅ ፕሮጀክት መኖሩን የገለጹት የፕሮግራሙ አስተባባሪና ሃላፊ አቶ አላዩ መኩሪያ ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ ከሶስት ነጥብ አራት ሚሊየን ይሮ በላይ መመደቡን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የፕሮጀክቱ ሃምሳ ፐርሰንት መጠናቀቁን ገልጸው ከዚህ ፕሮጀክት ውስጥ በምዕራብ ሃረርጌ ሚደጋ ቶላ ኡርጂ ሌንጫ ቀበሌ ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉ እና በድርቅ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና እንስሳት መልሶ ማቋቋም ስራ እየተሰራ ሲሆን በዋናነት የውሃ ቦኖዎችን በመጠገን፣የገንዘብ ቁጠባን በማስተማር፣የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር፣ለትምህርት ቤቶች መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት፣ምርጥ ዘር አቅርቦትና ለእርባታ የሚሆኑ ፍየሎችን እስከ መኖ የመስጠት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የኡርጂ ሌንጫ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አስከ ሶስት መቶ ሃምሳ ሜትር ጥልቀት የሚቆፈር ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ሶስት ቀበሌዎችን የውሃ ችግር እንደሚቀርፍ ተገልጿል፡፡ በሌሎች ቀበሌዎችም መሰረታዊ የህዝቡ ችግር ውሃ በመሆኑ ይህንን ለመቅረፍ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የውሃ ቦኖዎችን በመጠገን ከሃያ አራት ሺህ በላይ የአከባቢውን ነዋሪዎች ችግር መፍታቱን መመልከት ተችሏል፡፡
ድርጅቱ በሚደጋ ቶላ የእርሻ እቀባ የሚባል አዲስ ቴክኖሎጂን ለመጀመሪያ ግዜ በማስተዋወቅ የገበሬውን ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻላቸውን ገልጸው ከእርሻ ጎን ለጎን ለስድስት መቶ አርባ አራት አባወራዎች በድምሩ ሶስት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ፍየሎችን እስከነ መኖአቸው በመስጠት ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል፡፡

ሴቶች ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እንዲቆጠቡ እና በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት ሁለት መቶ ሰማንያ ስምንት ሴቶችን በአራት ማህበር በማደራጀት ቁጠባ እንዲጀምሩ ማድረግ እና የንጽህና አጠባበቅ ስልጠናን መሰረት ያደረገ ለአንድ ሺህ አራት መቶ አርባ እማወራዎች የውሃ ማጣሪያ ለግሷል፡፡
በአከባቢው ሰልጠናውን ያገኙ እና የቁጠባ አባል የሆኑት ወ/ሮ ከድጃ ኢብራሒም እንደገለጹት ድርጅቱ በሰጠን ስልጠና እዚህ አከባቢ የነበርን ሴቶች ከጨለማ ወደ ብርሃን መጠናል፤ መብታችንን በደንብ አውቀናል፤ ሴቶች ልጆቻችንን ያለእድሜ እንዳይዳሩ እንከላከላለን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቀናል በተለይም በየሳምንቱ በምናደርገው ውይይት የማህበራዊ ህይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ነው ያመጣልን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ የማህበረሰቡ የሁልግዜ ጥያቄ የሆነውን የውሃ ችግር ለመቅረፍ የሰራቸው ስራዎች በጣም አበረታች መሆኑን ገልጸው ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ በሌሎች አከባቢዎችም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋ፡፡


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ትምህርት ለልማት ለተባለ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የፈንድ ድጋፍ አደረገ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ትምህርት ለልማት ከተባለ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር የሶስት ሚሊየን ብር የፈንድ ድጋፍ ስምምነት አድርጓል፡፡ ባለስልጣኑ የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶችን የመደገፍና የክትትል ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ትምህርትን ማዕከል በማድረግ የተለያዩ የልማትና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፎች ላይ ትኩረት አድርጎ ለሚሰራው ትምህርት ለልማት ለተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የፈንድ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የስምምነት ሰነዱን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት የድርጅቱ የፕሮግራም ኃላፊ አቶ ቶቾ ኢንኮሶ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያገኙትን ድጋፍ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ በሎ ቀበሌ ላይ በመጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች እንደሚያውሉት በመግለጽ በአጭር ጊዜ ለማድረስ በአካባቢው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ድርጅቱ ቀደም ሲል በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከተመሰረተበት 1991 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት፣ በጤና፣ እና በልማት ስራዎች ላይ እንዲሁም በሰላም ግንባታ ላይ ለረጅም ጊዜ ሲሰራ መቆየቱን አንስተው በአካባቢው በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፈሎች የአስቸኳይ የምግብ እህል ድጋፍ ለማድረግ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር ስምምነት ላይ እንደደረሱ ጠቁመዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ አስተዳደርና ንብረት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መስቀሉ መንበሩ እንደገለጹት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በመደገፍና ከፈንዱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ አቅም ውስን ቢሆንም ያለውን ውስን ሃብት በአግባቡ በመጠቀም የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም ፈንዱ የሚጠናከርበትን መንገድ በመቀየስ በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለሁለት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሽከርካሪ ድጋፍ አደረገ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለሁለት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሽከርካሪ ድጋፍ አደረገ፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርገው ለሚሰሩ ሁለት ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሸከርካሪ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱን ጨምሮ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አስረክበዋል፡፡
ድጋፍ ከተደረገላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ ትኩረት ለሴቶችና ህጻናት ማህበር አንዱ ነው፡፡ የማህበሩ መስራችና ዳይሬክተር ሲስተር አሳየች ይርጋ ድርጅታቸው ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸው ህጻናትና እናቶቻቸውን መደገፍ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት መሆኑን ጠቁመው 164 ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ህጻናትና እናቶቻቸውን እየደገፈ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
ድርጅቱ በኢትዮጰጳያ የመጀመሪያ የሆነውን የልዩ ፍላጎት ማዕከል የገነባ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሯ ራቅ ካሉ አካባቢዎች ወደ ማዕከሉ ልጆቻቸውን ይዘው የሚመጡ እናቶች በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ቀስ በቀስ እየቀነሱና ህጻናቱም ለከፍተኛ የጤና መቃወስ እየተጋለጡ ስለመጡብን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቦታው ድረስ ሄዶ ችግሩን አይቶ ድጋፍ እንዲያደርግልን በጠየቅነው መሰረት ይህን የተሸከረካሪ ድጋፍ አግኝተናል ብለዋል፡፡
ሌላው ድጋፉን ያገኘው መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተመዝግቦ በሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ መሰረት አዛገ እንደገለጹት ድርጅቱ ለጎዳና ህይወት የተጋለጡ ህጻናትን ከጎዳና ላይ በማንሳት ማቋቋም ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጂንካ ከተማ ያለውን ፕሮጀክታቸውን በማየት እና ያለባቸውን የፋይናንስና እና የቁሳቁስ እጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሸከርካሪና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቁመዋል

ድርጅቶቹ ከሚሰሩት ስራ ስፋትና አስቸጋሪነት የተነሳ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደነበርና ይህንኑ ችግራቸውን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መስክ ድረስ ሄደው እንዳዩ የጠቆሙት የድርጅቶቹ ኃላፊዎች ድጋፉ በተሸከርካሪ በኩል ያለባቸውን ችግር የሚፈታላቸው መሆኑን ጠቁመው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን አመስግነዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ አስተዳደርና ንብረት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ መስቀሉ መንበሩ የተሸከርካሪ ድጋፉን በተመለከተ ባደረጉት ገለጻ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለይም ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን መሰረት አድርገው ለሚሰሩ ሀገር በቀል ድርጅቶች በአዋጅ ቁጥር 1113/11 መሰረት ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው በማንሳት ይህንኑ መነሻ በማድረግ ድርጅቶቹ ካለባቸው መሰረታዊ የግብዓት ችግር አንጻር እና ከሚሰሩት ሰፊ ስራ እንዲሁም የሚደርሱበትን የማህበረሰብ ክፍል መነሻ በማድረግ ድጋፉ ሊደረግላቸው እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለነዚህ ድርጅቶች ካደረገው የተሸከርካሪ ድጋፍ ባለፈ፤ ዳግም ምዝገባ ባለማድረጋቸውና ሪፖርት ባለማቅረባቸው ከተዘጉ እንዲሁም በፈቃዳቸው እንዲዘጉ ካመለከቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተገኙ የተለያዩ ንብረቶችን ልዩ ድጋፍ በሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ለሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያለባቸውን የግብዓት ችግር ክብደት መሰረት በማድረግ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የውጭ እርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ መሰማራት እንዳለባቸው ተገለፀ።

ይህ የተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮች ሰላም የህፃናት መንደር በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ እያከናወነ ያለውን ስራ በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡ ሰላም የህጻናት መንደር ከተመሰረተ ከ30 ዓመት በላይ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ድርጅት ሲሆን በዋናነት በህጻናት ማሳደግ ፣ በጤና እና በትምህርት ዙሪያ ፕሮግራሞች በመቅረጽ በሁለት ግቢዎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ጯሊ ገልፀዋል፡፡ ስራ አስኪያጁ አክለውም ድርጅቱ በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ የባለስልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው መጎብኘታቸው ጥሩ ስሜት እንደፈጠረላቸው በመግለፅ በቀጣይ ድርጅቱ ለመስራት ያቀዳቸውን ስራዎች በትጋት አንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
ሌላው ያነሱት ሰላም የህጻናት መንደር ህጻናትን ከማሳደግ ጎንለጎን የውጭ እርዳታ ከመጠበቅ በአገር ውስጥ የገቢ ማስገኛ ሰራዎችን እየሰራን አቅማችን በማሳደግ ድርጅቱን እያንቀሳቀሱ መሆኑን በመግለጽ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አቅማቸውን ለማሳደግ የውጭ እርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ ተሰማርተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ሰላም የህጻናት መንደር በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን በመግለጽ ሰላም የህጻናት መንደር ብቻ ሳይሆን በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ ተሰማርቶ በርካታ የልማት ስራዎችን እየሰራ ያለ ድርጅት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ም/ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ሰላም የህጻናት መንደር በስራ እድል ፈጠራ እና በሌማት ትሩፋት ላይ እያከናወነ ያለው ስራ መንግስት ከመደገፍ አንጻር ትልቅ ስራ እየሰራ መሆኑ በማንሳት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያቅደቸው እቅዶች ከመንግስት ከሚያቅዳቸውን እቅዶች ጋር የተናበቡ መሆን ሲችሉ ለአገር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ ተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እንዳሉት ሰላም የህጻነት መንደር ከተመሰረተ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ደርጅት መሆኑን በመጥቀስ በአሁን ወቅት ህጻናት ከማሳደግ ጎንለጎን በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ እያከናወነ ያለው ስራ የሚያበረታታ መሆኑን በመግለጽ ሌሎች አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰላም የህጻናት መንደር በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ እያከናወነ ያለውን ልምድ መውሰድ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ሌላው ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ መንግስት የጀመረውን የሌማት ትሩፋት ህብረተሰቡ በምግብ ራሱን እንዲችልና ከተረጂነት እንዲላቀቅ ከማድረግ አንጻር መንግስት የጀመራቸው ስራዎች ከማስቀጠል አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የሚበራታቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሰላም የህጻናት መንደር በገቢ ማስገኛ ስራ ላይ የሚያከናውናቸውን ስራዎችን ለማጠናከር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከጎናቸው እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ ሰላም የህጻናት መንደር በእንሰሳት ሀብት ፣ በግብርና በእንሰሳት መኖ ማቀነባበር እና በሌሎችም የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል፡፡


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍ ኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመሆን በሰላም ግንባታ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት የሲቪል ማህበረሰበ ድርጅቶች ስተዋጽኦን በሚመለከት ስልጠና ተሰጠ ።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍ ኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመሆን በሰላም ግንባታ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት የሲቪል ማህበረሰበ ድርጅቶች ስተዋጽኦን በሚመለከት ስልጠና ተሰጠ ።

የስልጠናውንም መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍ ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ ባስተላለፉት መልዕክት ድርጅታችን ባለፉት በርካታ አመታት በሰላም ግንባታ ፣በሰብአዊ መብቶች እና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በሚከሰቱ ግጭቶች ዙርያ እርቅ ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረው በዚህም ሂደት በርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ድርጅቱ ይዞት የተነሳውን ራዕይ እና እራሱን ችሎ ለመቆም ያደርግ የነበረው ትግል ለዚህ ስኬት አድርሶታል በማለት ሌሎች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ሲመሰረቱ ራዕይ ሊኖራቸውና እራሳቸውን ችለው መቆም የሚችሉበትን መንገዶች በማመቻቸት ለማህበረሰቡ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት መስጠት ይኖርባቸዋልም ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በስልጠናው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ባለስልጣን መስሪያቤቱ በአዋጅ ከተሰጡት ተግባራት መካከል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን መመዝገብ፣መከታተልና መደገፍ በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረው ይህም ስልጠና የዚሁ አካል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሰላም ግንባታ ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት መወጣት እንዲችሉ ስልጠናው ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡
ስልጠናውን ከባለስልጣን መስሪያቤቱ ጋር ያዘጋጁትን ጀስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጵያ ምስጋና አቅርበው ከስልጠናው በኋላ በተግባርም በሰላም ግንባታ ላይ የሴቶች ተሳትፎን ለማሳደግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባችሁ ብለዋል ።
በስልጠናውም ላይ ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተወጣጡ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጨምሮ የባለስልጣን መስሪያቤቱ የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል ።

Click the button

አንጋፋ ጋዜጠኛ ብርቱካን ሃረገወይን እና አቶ ወንደሰን አንዱዓለም የተቋሙ የንባብ ቀን አምባሳደር ሆነው ተሰየሙ፡፡

አንጋፋ ጋዜጠኛ ብርቱካን ሃረገወይን እና አቶ ወንደሰን አንዱዓለም የተቋሙ የንባብ ቀን አምባሳደር ሆነው ተሰየሙ፡፡

በተቋም ደረጃ የማንበብ ባህል በሰራተኞች ዘንድ እንዲዳብር ብሎም የሰራተኞች የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲያጠናክር ማድረግን ዓላማ ያደረገ ተቋማዊ የንባብ ቀን በየወሩ ይካሄዳል፡፡
በዚህ ፕሮግራም ላይ አንጋፋ ደራሲያን፤ማንበብን ባህላቸው ያደጉ ግለሰቦች፣ልምድ ያላቸው አካላት ቀርበው ተሞክሯቸውን ለሰራተኞች የሚያካፍሉ ሲሆን የተለያየ ተሰጥኦ ያላቸው ሰራተኞችም ስራቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ነው፡፡
በዛሬው የአስራ ሁለተኛ ወር የንባብ ቀን ልምዳቸውን ያካፈሉን ለሃያ ስድስት ዓመታት በጋዜጠኝነት ያገለገሉት ወ/ሮ ብርቱካን ሃረገወይን እና የተለያዩ የህትመት እና የቴሌቭዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ፤የብርሃን አህማድ የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲ አቶ ወንደሰን አንዱዓለም ሲሆኑ የተቋሙ የንባብ ቀን እምባሳደር በመሆንም ተመርጠዋል፡፡
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ባስተላለፉት መልዕክት የተቋሙን ሰራተኞች የመፈጸምና የማስፈጸም አቅማቸውን ለማጎልበት የተለያዩ ተግባራትን ተቋሙ እንደሚያከናውን ገልጸው ሰራተኞች በማንበብ የሚያገኙትን እውቀት ለማጎልበትም እንደዚህ አይነት ፕሮግራም ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል፡፡
አያይዘውም ልምዳቸውን ለማካፈል በተቋሙ ለተገኙ አካላት እንዲሁም ለተቋሙ ቤተ መጽሐፍት ግብዓት ለማሟላት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዋጽኦ ላደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ PAD የተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሃምሳ (50) በአማርኛና በእንግሊዘኛ የተጻፉ መጽሐፍቶችን ለተቋሙ ቤተ መጽሐፍት በስጦታ አበርክተዋል፡፡

Click the button