የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን volunteer services overseas (VSO) ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃድና የበጎ ፈቃድ መረጃ አስተዳደር ስርዓት (VMIS) ዙሪያ ስልጠና ሰጠ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከ VSO ጋር በመተባበር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአምስቱ ካንፓሶች ለሚገኙ ተማሪዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽንሰ ሃሳብና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሙያዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እገዛ የሚያደርገውን የበጎ ፈቃድ መረጃ አስተዳደር ስርዓት (VMIS) በሚመለከት ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህ እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ህክምና አገልግሎት ምክትል ኮርፖሬት ተወካዮች እና በአምስቱ ካንፓሶች የሚማሩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው የትምህርትና ህክምና አገልግሎት ምክትል ኮርፖሬት ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ሙሉቀን ብርሃኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ትኩረት ማግኘት በመቻሉ ተማሪዎች ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያላቸውን ተነሳሽነት የሚያዳብር መሆኑን ጠቁመው መሰል ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች የተማሪዎችን አቅም በማጎልበት ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎች በተማሪዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ተወካዩ ከስልጠናው በኋላ ተማሪዎች ቀደም ሲል ይሰጡት ከነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሻለ ውጤታማ ስራ መስራት እንዲችሉ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ሀገራት ወደተሻለ ስልጣኔ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንስተው የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን የተላበሰ ማህበረሰብ ሀገርን በመገንባት ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የተላበሰ ማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ችግር እንደማይገጥመው ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ አብሮነትን፣ ህብረ ብሄራዊነትን ማዕከል ያደረገ፣ የሚተሳሰብ፣ እርስ በርስ የሚረዳዳ እና ሀገራዊ ስብራቶችን ለመጠገን በጎ ፈቃድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው የጠቆሙ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎች የበጎ ፈቃደኞች መሰባሰቢያ እና ማዕከል እንዲሆኑና ሀገር ከበጎ ፈቃደኞች ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ እንድትሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዳማ፣ ወራቤ፣ ወልቂጤና አሁን ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ የጠቆሙ ሲሆን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ይኸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የበጎ ፈቃደኞች ማዕከል እንዲሆን እንፈልጋለን ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ክበቦችን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በከተማው ውስጥ በሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን በመስጠትና በዩኒቨርሲቲው ውስጥም ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን በመከወን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡ እሴት እንዲሆን የበኩላችሁን እንድትወጡ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምንነትንና ጽንሰ ሀሳብን በሚመለከት ስልጠናውን የሰጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ትብብር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሉላ ሚሊዮን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር መካከል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማህበረሰቡ ውስጥ ባህል እንዲሆን ማስቻል መሆኑን ጠቁመው ስልጠናው በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሙያቸው እና በተማሩበት የትምህርት መስክ የሙያ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግላቸው አንስተዋል፡፡
ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን የተሰጠውን ስልጠና ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር ያዘጋጀው ከባህር ማዶ በጎፈቃድ አገልግሎት ድርጅት ወይም በእንግሊዘኛው አጠራር volunteer services overseas (VSO) በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ድርጅት ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ጌታያውቃል አብርሃም ድርጅቱ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ በበጎ ፈቃድ፣ በተቀናጀ ልማት፣ በትምህርትና አቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸው ከስልጠናው በኋላም በዩኒቨርሲቲው ለሚገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ክበባት ትስስርe በመፍጠር ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል፡፡ በስልጠናው ላይ volunteer services overseas (VSO) በኢትዮጵያ ውስጥ እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን በጎ ፈቃድን በማህበረሰቡ ውስጥ የማስረጽና ባህል የማድረግ ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት መሰል ስልጠናዎችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የበጎ ፈቃድ ክበባትን የማጠናከርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡












