የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ 1113/2011 በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት የበጎ ፈቃደኝነት ባህልና እንቅስቃሴ ማበረታታት፣ የበጎ ፈቃደኝነት በተመለከተ የስርፀት ስራ መስራት ነው፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሰጠውን ሀላፊነት ለመወጣትና የበጎ አድራጊነት እና የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን በህብረተሰብ ውስጥ ባህል ለማድረግ የበጎ ፈቃድ ስርፀት አመራር ማንዋል ላይ በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጅግጅጋ ከተማ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት አመራሮች ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደተናገሩት አገራችን በለውጥ ጎዳና ውስጥ ከገባች አንስቶ በዋናነት ለውጥ የተደረገው በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡: አያይዘውም ዘርፉ በቀድሞ ህግ የዜጎች የመደራጀት መብት የተገደበበት፣ በሰብዓዊ መብትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ መሰራት የተከለከለበት፣ እንዲሁም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የነበረው አተያይ የተዛባ እንደነበር በመግለጽ አገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ መቅረቷን አንስተዋል፡፡
በለውጡም ማግስት በመንግስት የተወሰደው እርምጃ አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን አዋጅ ሙሉ በሙሉ በመለወጥ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ከፖለቲካ ወገኝነት ነጻ የሆኑ በአገሪቱ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ እና አስተዋጾ እንዲያደርጉ እንዲሁም በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን የመደራጀት መብት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ም/ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ህብረተሰባችን የተጎዳ በመሆኑ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት ስራ የተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚሰራ ሳይሆን በዘላቂነት አጠናክሮ መስራት አስፈላጊ መሆን እንዳለበት በመግለጽ በጎ የሚያደርግ ሰው ክፋት የለውም ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡
በጎ ፈቃደኝነት ስራን ተቋማዊ ለማድረግ በህግ መደገፍ አለበት፤ፖሊሲም እየወጣ ነው፤ ባለስልጣኑም ማንዋል በማዘጋጀት በየክልሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡ በስልጠናው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሶማሌ ክልላዊ መንግስት የፋይናንስ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙህዲን አብዲ እንዳሉት ይህን ስልጠና በክልላችን ለመስጠት በመምጣታችሁ ደስተኛ ነን በማለት የባለስልጣን መስሪያቤቱ ድርጅቶችን ከመመዝገብ ባሻገር የሚሰሩ ስራዎችን በመቆጣጠርና መከታተል እንዲሁም እውቅና መስጠት አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በጎ አድራጊነት ድንበር የለውም ያሉት ቢሮ ሀላፊው በዋናነት መንግስትም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ህዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል፡፡