ዳግም ምዝገባ ባላደረጉ 1558 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችናህልውናቸውን ባላረጋገጡ 296 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ቦርድ አስታውቋል፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር በመተባበር በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት ዳግም ምዝገባ ባላደረጉ እና የ2013 በጀት አመት ሪፖርት ያላቀረቡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በተመለከተ ውይይት ለማድረግ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ በመድረኩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢና የፕላንና ልማት ሚንስቴር ሚንስትር ደኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃና ወልደገብርኤል እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል፡፡ አዋጅ 1113/2011 መሰረት በቀድሞው አዋጅ 621/2001 የተመዘገቡ ድርጅቶች በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ቀርበው መመዝገብ እንዳለባቸው የሚደነግግ ሲሆን በዚሁ መሰረት 1558 የሚሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዳግም ባለመመዝገባቸው እና 296 ድርጅቶች ህልውናቸውን ባለማረጋገጣቸው ለባለስልጣኑ ቦርድ ለውሳኔ ማቅረቡን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ገልጿል፡፡

May be an image of 1 person, table, dais and text that says 'RESERVED'

በዚህም መነሻነት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት አባላት ጋር ውይይት እንዲደረግ አቅጣጫ ማስቀመጡ በመድረኩ ተገልጿል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት ሪፖርት በማቅረብ ህልውናቸውን ባላረጋገጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የመጨረሻ ውሳኔ ሚያዚያ 20/ 2016 ዓ.ም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ቦርድ ውሳኔ እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን በሚቀጥሉት 30 ቀናት ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቀርበው ሪፖርት እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከአንድ አመት በላይ ዳግም ያልተመዘገቡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዳግም እንዲመዘገቡ በተለያየ መልኩ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርግም መመዝገብ ያለመቻላቸውን ተገልጾ አሁን ቦርዱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሪፖርት ማያደርጉ ከሆነ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመጨረሻ የተባለውን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም በመድረኩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቦርድ ጽህፈት ቤት መመሪያ ቁጥር 970/2015 መሰረት የተቋቋመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚቀርቡ የይግባኝ ጥያቄዎችን በመመሪያው መሰረት በመቀበል እልባት የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡