የመርሃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ባስተላለፉት መልዕክት የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶችና ሀገራዊ አንድነትንና ብሔራዊ መግባባትን በሚያጠናክሩ ሁነቶች እየተከበረ መቆየቱን ገልጸው በዘንድሮ ዓመትም ለ19ኛ ጊዜ በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነትና አስተባባሪነት በመላ ሀገሪቱ “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል በድምቀትና በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ዓላማውም ስለ ሰንደቅ ዓላማ ምንነት፣ ክብርና ትርጓሜ በተገቢው መንገድ ዜጎች አንዲረዱ በማድረግ ለሀገራችን ሉዓላዊነት፤ለነጻነት እና ለሰንደቃችን ክብር የተደረገውንና እየተደረገ ያለውን ተጋድሎ ተገቢውን እውቅና በመስጠት የጋራ ሀገራዊ መግባባት እና ሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነት በማጠናከር ብሔራዊ አንድነትን ማፅናት መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
የባንዲራ ቀን ሲከበር በአዲስ መንፈስ እና በጸና ማኅበራዊ ውል የተመሰረተው የመደመር መንግሥት በተመሰረተበት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ እየገነባች ያለውን የብልጽግና ስኬቶች ይበልጥ ለማጠናከር እና ሁለንተናዊ ከፍታዋን ለማረጋገጥ የተቀየሰ ትልቁ ሀገራዊ የሽግግር ምዕራፍ በመሆኑ ሁሉም ሰራተኛ ለተፈጻሚነቱ መትጋት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የባንዲራ ቀንን ስናከብር ደንበኞችን በአግባቡ ለማገልገል ቃል በመግባት እና የሃገራችንን የከፍታ ጉዞ በማሳብ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው የመንግስት ሰራተኛው ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የመንግስትን ህግና ደንብ በማክበር፤ የተሰጠንን የመንግስት ስራ በቁርጠኝነት በመፈጸም የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ መስራት ይጠበቅባችኋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር እና ቃለ መሃላ በመፈጸም ተከብሯል፡፡



