በ15ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የክልልና የፌደራል ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባዔ ጉባዔ ላይ ከቀረቡ ሰነዶች አንዱ “የሲቪል ማህበራት ሚና በ7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የነበራቸውን አስተዋጽዖ የሚገልጽ ነው፡፡

ሰነዱን ያቀረቡት የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕረዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን ሲሆኑ ባቀረቡት ሪፖርትም ከ200 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በ7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ጊዜና የድህረ ምርጫ ተግባራትን ለመከወን በምርጫ ቦርድ ፍቃድ ማግኘታቸውን እና ከዚህም ውስጥ 114 የሚሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ አግኝተው በመራጮት ትምህርትና በመታዘብ ስራዎች ላይ መሳተፋቸው አብራርተዋል፡፡

አክለውም በምርጫ ቦርድ ፈቃድ ካገኙ እና በምርጫ ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተከታታይነት ያለው ውይይትም መደረጉን አብራርተው የሲቪል ማህበራቱ ታዛቢዎችን በመመልመልና ስልጠና በመስጠት፤ ለሚዲያ ተቋማት ምርጫ አዘጋገብን ስነምግባርን በተመለከተ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ታዛቢዎችን ማሰማራት እና መታዘብ እና መሰል ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከምርጫው በኋላም በምርጫው ሂደት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላደረጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምክር ቤቱ አዘጋጅነት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝደንት እና ሌሎች በርካታ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የምስጋናና የእውቅና መርኃግብር መካሄዱን አንስተው 7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ተዓማኒ፣ ፍትሀዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አይነተኛ ሚና እንደነበራቸው ጠቁመዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ በሰጡት አስተያየት ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንዱ መሳሪያ ምርጫ መሆኑን ጠቁመው ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊና ፍትሀዊ ምርጫ ለማከናወን በርካታ ጫናዎች ነበሩ ብለዋል፡፡ አያይዘውም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው መንግስት የሚደራደርበት ጉዳይ እንዳልሆነ አንስተው በዚህ ረገድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ጠንካራ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዬች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በበኩላቸው የዘንድሮው ምርጫ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአጠቃላይ ምርጫን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማገዝ መደገፍና ክፍተት ሲኖር ክፍተቱን ማሳየት መቻላቸቸውን ያሳየ መሆኑን አድንቀው በ7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ዘርፉ ከነበረበት ድባቴ ወጥቶ ገንቢ የሆነ ሚና መጫወት መቻሉን ገልጸዋል፡፡