የሲቪልማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሴት ሰራተኞች ፎረም የ2018 በጀት ዓመት እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን በውይይቱ ላይ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ትዕግስት አቡዬ እና የፎረሙ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ በፎረሙ ጉባዔ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተቋሙን ሴት ሰራተኞች አቅም በማጎልበት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተጋ እንደሚገኝ ጠቁመው በጋራ በመንቀሳቀስ ውጤታማ ሴቶችን ወደፊት በማምጣት የሚያጋጠሟቸውን ችግሮች በመቅረፍና የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተቋሙ አመራሮች ከፎረሙ ጎን እንደሚቆሙ ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በንግግራቸው ለፎረሙ አባላት እና አመራሮች እንዲሁም ለፎረሙ ውጤታማነት ጉልህ ድርሻ ለነበራቸው ሴት ሰራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሴቶች ፎረም ባለፈው በጀት ዓመት የተቋሙን ሴት ሰራተኞች አቅም የሚያጎለብቱ ተግባራትን ሲያከናውን የቆዬ መሆኑ በሪፖርቱ የተገለፀ ሲሆን “እኔም ሀሳብ አለኝ” በሚል መሪ ሀሳብ የተቋሙ ሴት ሰራተኞች ሀሳባቸውንና ልምዳቸውን ሲለዋወጡ መቆየታቸው ተገልጿል። በመድረኩ የፎረሙ የኦዲት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ለፎረሙ ነባር አመራሮች ሽኝት እና የአዳዲስ የፎረም አመራሮች ምርጫ ተከናውኗል። በተጨማሪም በፎረሙ የስራ እንቅስቃሴ ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አባላት የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።