በጉባዔው ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉት የሲቪል ማህበራት የሕዝብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ፣ የልማት አጋርነታቸውን በማሳየት እና ማህበረሰቡን በማንቃት ረገድ ያላቸው ድርሻ የሚተካ አለመሆኑን አንስተው ይህንን ሚናቸውን ከግብ ለማድረስ ዘላቂነትን ማረጋገጥ፤ ከመንግስት እቅድና ስትራቴጂ ጋር መናበብ፤ በተቀናጀና በትብብር መንፈስ መንቀሳቀስ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል። አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የተጀመረው ሪፎርም በሂደት ላይ ብቻ ሳይወሰን የበለጠ እየተጠናከረ እንዲሄድ ሰፊ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝና በቀጣይም ዘርፉን ለማጠናከር የሚያስፈልገውን ተገቢ የድጋፍ፣ የክትትልና አጠቃላይ የአመራር ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተው 15ኛው የጋራ ጉባኤም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር እንዲጠናከር እና አገራዊ ፋይዳውን እንዲያጎለብት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው ሲሉ ገልፀዋል።



በተለይም ሪፎርሙን በሁሉም ክልሎችና መዋቅሮች በውጤታማነት ለማውረድ እና ያሉ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት አይነተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ይህንን ቅንጅትና መስተጋብር አጠናክረን መቀጠል እንደሚገባ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አፅንዖት ሰጥተዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ በበኩላቸው ዘርፉ በሚጠበቅበት ልክ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እስከታችኛው መዋቅር ድረስ መከታተል እና መደገፍ እንደሚገባ ጠቁመው የተመዘገቡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መሆኑን መገምገም እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2019 እቅድ በስራ አመራር ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል ግዛው ቅርብ ውይይት ተደርጎበታል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በ7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ የነበራቸውን አስተዋፅዖና የተከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን የቀረበ ሲሆን የክልል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከ14ኛው ጉባዔ በኋላ የሰሯቸውን አጠቃላይ ስራዎችና በዴስክ ሀላፊዎች ውይይት የተጠናቀሩ ጉዳዮችን የዳሰሰ ሪፖርት ቀርቧል። በተጨማሪም የባህር በር አስፈላጊነትን በተመለከተ በውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ተወካይ እንዲሁም ቅን ልብ የሞባይል መተግበሪያን በተመለከተ በባለስጣኑ የበጎ ፈቃድና ትብብር መሪ ስራ አስፈጻሚ አስተባባሪ ገለፃ ተደርጓል።




