


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከክልል የፋይናንስ እና ፍትህ ቢሮ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዴስክ ኃላፊዎች ጋር የሚያደርገው ውይይት በአዳማ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በውይይት መድረኩ ላይ ከሁሉም ክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዴስክ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ የተሰሩ ስራዎችና በስራ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት ዘርፉ የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት በበለጠ ለማረጋገጥ የሚችልበትን የመፍትሄ ሀሳብ ለማቀረብ እንዲሁም ዘላቂ ትብብርን ለማጠናከር የሚደረግ ሲሆን በውይይቱ የሚቀርቡ የመፍትሄ ሀሳቦች ተጠናቅረው በ15ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የክልልና የፌደራል ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባዔ ላይ የሚቀርብ ይሆናል።
በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ያመጡት ውጤት እንዲሁም በስራዎቻቸውም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉት የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ምን እንደሚመስሉ በውይይቱ ተዳሷል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሁሉም ክልሎች በመዘዋወር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ጥቅል መረጃ ከ14ኛው ጉባዔ በኋላ ያሰባሰበ ሲሆን በሂደቱ የታዩ ክፍተቶችንና በመረጃ አያያዝ ረገድ የታዩ ችግሮችን በመለየት የቀረቡ ምክረሃሳቦች በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የውጪ ድርጅቶች ክትትል ምርመራና ግምገማ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሉላ ሚሊዮን አቅርበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ላነሷቸው ጥያቄዎችና ማብራሪያዎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ክትትል ግምገማና ምርመራ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተሾመ ወርቁ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ኃ/ሥላሴ ገ/ሚካኤል እንዲሁም የየስራ ክፍሎቹ ሃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ውይይቱ በክልሎች መካከል የልምድ ልውውጥ ባህልን በማሳደግ ረገድ ጉልህ አስተዋፅዖ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በዘርፉ ላይ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን በየጊዜው በመለየት የተሻለና የተቀላጠፈ አሰራር ለመዘርጋት እገዛ እያደረገ ይገኛል።

