የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተቋማዊ የንባብ ቀን እና የ2019 አዲስ ዓመት መባቻ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ፣ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ፣ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ እና የተቋሙ አመራሮች እንዲሁም ሰራተኞች በተገኙበት በድምቀት ተካሂዷል፡፡ በመርኃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ተቋማዊ የንባብ ቀን መርኃ ግብሩ ላይ በርካቶች መጥተው ልምድና ተሞክሯቸውን ያጋሩበት መድረክ መሆኑን አስታውሰው ህብረ ብሄራዊነታችንን ባንጸባረቀ መልኩ የተካሄደው 15ኛው ዙር ተቋማዊ የንባብ ቀን በአዲሱ አመት ተቋማችን ለማሳካት ያቀዳቸውን እቅዶች ወደተግባር ለመቀየር የምንተጋበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አዲሱ ዓመት እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደፊት የምንሄድበት፤ እቅዶቻችንን ወደተግባር ለመለወጥ ታጥቀን የምንነሳበት ብሩህ ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው የለውጡ አንዱ ስኬት የተቋማት ግንባታ መሆኑን ጠቁመው ባለስልጣኑ በዚህ ረገድ ያመጣው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አሁን ያለው የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን የንባብ ባህላችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እያደረገ ባለበት ወቅት እደዚህ አይነት መርኃ ግብሮች አስተሳሰብን ለመቅረጽ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡ በተቋሙ የተለመደው ባህል በሌሎች ተቋማትም እንደአርአያ የሚወሰድ መሆኑን በመጠቆም የዲጂታል ሚዲያውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀየር ማንበብ ትልቅ ድርሻ እንዳለውም አክለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተቋማዊ የንባብ ቀን ለተከታታይ 15ኛ ጊዜ በልዩ ልዩ መርኃ ግብሮች ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በዚህኛው ዙር ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በተውጣጡ የተቋሙ ሽማግሌዎች ምርቃት፣ በተለያዩ የስነጽሁፍ ዝግጅቶችና የአበባየሆሽ ጨዋታ በድምቀት ተካሂዷል፡፡





