የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ Safe light initiatives በመባል የሚታወቀውን በወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ድርጅትን ጎበኙ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከባለስልጣኑ ከተለያየ የስራ ክፍሎች ከተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በመሆን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመዝገብ ቁጥር 4906 ተመዝግቦ በወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራውን Safe light initiatives የተባለውን ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የስራ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት ጉብኝት አድርገዋል፡፡ SAFE LIGHT በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ፣ በአመራርና የሙያ ድጋፍ፣ በዲጂታል ስርዓት ተሳትፎ እና ወጣቶችን ማብቃት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን የተቋቋመውም በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2018 በአምባሳደር ስለሺ ሳልስ ኡመር አማካኝነት ነው፡፡
ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑና ዓለምአቀፍ ልምድና ተሞክሮ እንዲያገኙ እንዲሁም የአመራርና የስራ ፈጠራ አቅማቸው እንዲዳብር የሚያደርጉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የድርጅቱ መስራችና ዳይሬክተር አምባሳደር ስለሺ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ድርጅቱ ወጣቶችን መሰረት አድርጎ የሚሰራ በመሆኑ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱና ከሌሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የድርጅቱ የስራ እንቅስቃሴ እጅግ የሚበረታታና የሚደገፍ መሆኑን ጠቁመው ከሀገር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ ወጣቶችን እየተመለከትን ስለሆነ መደገፍና ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መሰል ድርጅቶችን ለመደገፍ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ለድርጅቱ ስኬት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡