በወላይታ የሚገኙ ጠረጤዛ ልማት ማህበር እና ቼንትሮ የተባሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህ ከሌሎች የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተሮች፣የክልሉ የሲማድ ዴስክ ዳይሬክተር እና ሌሎች የተቋሙ የስራ ክፍል ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ጠረጤዛ ልማት ማህበር ሃገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሲሆን በሃገራችን በተለያዩ አከባቢዎች በአከባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት በማድረግ ይሰራል፡፡
ድርጅቱ 16 ፕሮጀክቶች ስራ ላይ ያሉት ሲሆን ከአከባቢ ጥበቃ ስራ በተጨማሪ የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ስልጠና፣የህጻናት ጥበቃ ፣ጤና እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ይሰራል፡፡ የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በሰጡት አስተያየት ባለስልጣን መስሪያቤቱ ጠንካራ ሃገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲፈጠሩ ይሰራል ለዚህ ማሳያ ስለሆናችሁ ምስጋና ይገባችኋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡


አያይዘውም በባለስልጣን መስሪያቤቱም ሆነ በክልሉም ጥሩ አፈጻጸም ካላቸው ድርጅቶች መካከል በመሆናችሁ ይህንን ስራችሁን አጠናክራችሁ መቀጠል ይኖርባችኋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ቼንትሮ በኢትዮጵያ ከ43 ዓመት በፊት በጣሊያን ተወላጅ በሆኑት አቶ ሮቤርቶ የተመሰረተ ሲሆን ወላጅ አልባ እና የአካል ጉዳት ያለባቸውን ህጻናት በማዕከል የማሳደግ እና መሰረታዊ ግብዓት የሟሟላት ስራ ይሰራል፡፡ አሁን ላይ 130 በላይ ህጻናትን በማዕከል እንዲሁም ከ 3000 በላይ ህጻናትን በያሉበት እርዳታ እያደረገ የሚገኝ የሲቪለe ማህበረሰብ ድርጅት መሆኑ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

