የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና ባለድርሻ የመንግስት አካላት ጉባዔ ለ14ኛ ጊዜ በደቡብ ኢትዮጵያ ወላይታ ሶዶ ከተማ በድምቀት ተካሄደ። በጉባዔው ላይ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋን ጨምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ የመንግስት ተጠሪና የብልጽግና ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ ገ/መስቀል ጫላ እንዲሁም የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የየክልል ፍይናንስ እና ፍትህ ቢሮ ኃላዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
በጉባዔው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የፍትህ ሚንስቴር ሚኒስትር ደዔታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ እንዳሉት በሁለንተናዊ መልኩ የኢትዮጵያን ከፍታ በማረጋገጥ አገራችን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት የመሆን ውጥኗን እውን ለማድረግ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በከፍተኛ ደረጃ በትብብርና በአጋርነት ስራዎችን በጋራ አቅዶ መተግበር የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቁመው መንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገራዊ የፖሊሲ ቀረፃ፣ በልማት ስራዎች እና በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ እጅና ጓንት ሆኖ መንቀሳቀስ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል። አክለውም ከዚህ ቀደም የተጀመረውን ትብብርና ቅንጅት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚገጥሙ ተግዳሮቶች በግልፅ መነጋገርና መፍታት ይኖርብናል ያሉት ሚንስትር ደዔታው ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቁ በርካታ ኃላፊነቶች ያሉ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያ ከፍታ የሚረጋገጠው ሁሉም በየዘርፉ ተጠያቂነትና ግልፀኝነት የሰፈነበት አሰራር ሲከተል መሆኑን ጠቁመዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከማንም በላይ ለህዝብና ለህግ ተገዢ በመሆን ለዜጎች አርዓያ መሆን ይጠበቅባቸዋል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም በፍትህና በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ፣ በማስረጃ የተረጋገጠ፣ ገንቢና ለሀገራዊ አንድነት የሚበጅ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ተጠሪና የብልፅግና ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ክቡር አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና በባለድርሻ አካላት በየደረጃው የሚታዩ የቅንጅትና የትብብር ችግሮችን በመቅረፍና መተማመንን በመፍጠር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የመንግስት አጋር እንዲሆኑ የሚያስችል ተቋማዊ ጥንካሬና ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
የጋራ ጉባዔው የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥና ከመንግስትና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልጸዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መጪው አገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና መጫዎት እንደሚኖርባቸው ጠቁመው በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት ለዚህ ስራ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
አክለውም በ14ኛው ጉባኤ ባለስልጣን መ/ቤቱ መጪውን ምርጫ በተመለከተ ያዘጋጀውን እቅድ አቅርቦ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመው የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር ተግባራዊ የሚሆን መሆኑን ጠቁመዋል።
በጉባዔው ላይ የሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ መስተዳደር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዴስክ ኃላፊዎች በስድስቱ ወራት ያከናወኗቸውን ተግባራት እና ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች ከነመፍትሄ ሃሳቦች ጋር ሪፓርት ያቀረቡ ሲሆን ከምርጫ ጋር በያያዘ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የያዘውን እቅድ በሚመለከት ገለፃ ተደርጓል።
በተጨማሪም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ዴጌቲ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ራስን በራስ አስተዳደር በሚመለከት ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከሶሻል ኢንተርፕራይዞች ጋር በተያያዘ የቅድመ ጥናት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በመድረኩ ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሞክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እና በፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር ደዔታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ እንዲሁም በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሀሚድ ከኒሶ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ደዔታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ከዘርፉ ጋር በተያያዘ ያሉ ክፍተቶችን በማረም መረጃ የማጥራት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በተጨማሪም የተጀመሩ የቅንጅትና የትብብር ስራዎችን ማጠናከር እና ማስቀጠል ላይ ይበልጥ እንደሚሰራ ተጠቁሟል። ፕሮግራሙን በፍይናንስ ድጋፍ ያደረጉት WHH እና people in need ናቸው።