የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የሚያሳልጥ እና በጎ ፍቃደኞችን እውቅና የሚሰጥ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ ሆነ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከKorea International Volunteers organization ጋር በመተባበር በጎ ፈቃደኞችን የሚመዘግብና የሚያገናኝ እንዲሁም መረጃዎችን የሚያደራጅና የሚተነትን በአይነቱ ልዩ የሆነ “ቅን ልቦች(We Volunteer) የተሰኘ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ ( Mobile Application) የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው በጎ ፈቃደኞች በተገኙበት ይፋ አድርጓል፡፡

የሞባይል መተግበሪያውን በይፋ የመረቁት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ሚንስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ “ቅን ልቦች( We Volunteer) የሞባይል መተግበሪያ የበጎ ፈቃድ አገልገሎትን በማቀላጠፍና በጎ ፈቃደኞችን በማስተሳሰር ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አንስተው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በተደራጀ መንገድ በመምራት ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ከ3 ዓመት በፊት volunteerism management Information System /VMIS/ ለምቶ ወደ ስራ የገባ መሆኑን አንስተው አሁን ደግሞ “ቅን-ልብ” ወይም “We Volunteer” የሞባይል መተግበሪያን ከኮሪያ ኢንተርናሽናል ቮለንቲር ኦርጋናይዜሽን (KVO) ጋር በመተባበር በማልማት ወደ ስራ የገባ መሆኑን ጠቁመው ጥረቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ የመገንባት የመንግስት አቅጣጫ አካል ተደርጎ የሚወሰድ እና በአገራዊ የበጎ ፈቃደኝነት ባህል ማሳደግ ጥረት ውስጥ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት በጎ ፈቃደኝነትንና የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማህበረሰቡ ውስጥ የማስረጽና ባህል የማድረግ እንዲሁም የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ኃላፊነት ለመወጣት በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም እክለው ገልጸዋል።

የሞባይል መተግበሪያውን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት የKorea International Volunteers Organization-KVO) የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ሚኪያስ ግርማ በበኩላቸው የሞባይል መተግበሪያው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቁመው ተበታትኖ ይሰጥ የነበረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደአንድ ማዕከል በመሰብሰብ፣ በጎ ፈቃደኞች የሚሰጡትን አገልግሎት በመለካትና ለበጎ ፈቃደኞች ዕውቅና በመስጠት ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሲካው ሞላ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት ዘንድሮ ለ40ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፉን የበጎ ፈቃደኞች ቀን ምክንያት በማድረግ የሞባይል መተግበሪያው ይፍ መደረጉን አንስተው በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ዜጎች በቀላሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉና እውቅና እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም መተግበሪያው ወደ ስራ ሲገባ የመንግስት ባለድርሻ አካላት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና በጎ ፈቃደኞች መተግበሪያውን ማስተዋወቅና መጠቀም እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው በሂደቱ ተሳትፎ ለነበራቸውና ትብብር ላደረጉ የKorea International Volunteers Organization-KVO ኃላፊዎች እንዲሁም ለባለስልጣኑ ባለሙያዎች ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡