ሁንዴ ኦሮሞ የሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት በውኃ እና ሳኒቴሽን ስራ ከ13 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉ ተገለጸ፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ሁንዴ ኦሮሞ በጂማ ዞን ያከናወናቸውን ተግባራት በአካል ተመልክተዋል፡፡
ሁንዴ ኦሮሞ የሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን በጂማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ በሶስት ወረዳዎች እና በ10 ቀበሌዎች ላይ በውኃ እና ሳኒቴሽን ከ13 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገ የተቀናጀ ፕሮጀክት ለባለስልጣኑ የስራ ሃላፊዎች አስመልክቷል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት ውሃውን ለማህበረሰቡ በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ እና ለሴቶች የስራ እድል ለመፍጠር አስር ኪዎስኮችን በመስራት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ችለዋል፡፡
ሁንዴ ኦሮሞ ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ በግብርና እና በትምህርት ቤት ላይ ያከናወናቸውን ተግባራት አስጎብኝቷል፡፡


312 አርሶ አደሮችን አባል ያደረገው የጥቁሬ ገቢሳ የቡና ማቀነባበሪያ ላይ ድርጅቱ ለአርሶ አደሮች ከማሳ ጀምሮ የሙያ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ለማህበሩ የቡና መፈልፈያ ማሽን እና ሌሎች አስፈላጊ የሚባሉ ግብዓቶች በሟሟላት በኢኮኖሚ እዲጎለብቱ እና ምርትና ምርታማነት ከጥራት ጋር እንዲያድግ እየሰራ ይገኛል፡፡
በትምህት ቤቶች ላይ ልጃገረድ ሴቶች ንጽህናቸውን የሚጠብቁበት የተሟላ የንጽህና መጠበቂያ ስፍራ እስከ አስፈላጊ ግብዓት በማዘጋጀት ለሌሎች ትምህርት ቤቶች እንደመነሻ ተሞክሮ ተወስዶ እየተሰራበት መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
ሁንዴ ኦሮሞ በኦሮሚያ ክልል ብቻ በ16 ዞኖችና በ60 ወረዳዎች ላይ በግብርና፣በውሃና ንጽህና አጠባበቅ እና በትምርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ የሃገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡

