በሴቶችና ህፃናት መብቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የአቅም ግንባታ መድረክ ተካሄደ።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከጀስቲስ ፎር ኦል (JFA-PFE) ጋር በመተባበር በሴቶችና ህፃናት ላይ ትኩረት አድርገው ለሚሰሩ ህብረቶች በሴቶችና ህፃናት መብቶች እና በሎካላይዜሽን ላይ ትኩረት ያደረገ የአቅም ግንባታ መድረክ በJFA-PFE የስልጠና ማዕከል ተካሄደ።

በመድረኩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ JFA-PFE ኃላፊዎችና የየህብረቶቹ ተወካዮች ተገኝተዋል።

መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሙሉነህ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

እነዚህን ተልዕኮዎች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ከልዩ ልዩ ድርጅቶች ጋር ስትራቴጃዊ አጋርነቶችን በመፍጠር በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከ ጀስቲስ ፎር ኦል (JFA-PFE) ጋር በተለይም በሰብአዊ መብት፣ በሰላም ግንባታ፣ በወጣቶች፣ በሴቶችና ህጻናት ዙሪያ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ የአገር በቀል ድርጅቶችን አቅም የሚያጎለብቱ ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት እና በትብብር የሚሰሩበትን ሁኔታ የሚያጠናክሩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል።

መድረኩ የአገር በቀል ድርጅቶች አመራሮችን አቅም ለመገንባት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አንስተው ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የስልጠና ፕሮግራምም ድርጅቶች ዘላቂ የሆነ የገቢ ምንጭ ያላቸውና ከተረጅነት የተላቀቁ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚያግዙ ሃሳቦችን ለመለዋወጥ፣ የሴቶችና ህጻናት መብቶችን በተመለከተ ያሉ ህጎችን እንዲሁም የፕሮጀክት አዘገጃጀት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ የሚያገኙበት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አቶ ፋሲካው ሞላ ሎካላይዜሽንን (Localization) በሚመለከት ገለጻ ያደረጉ ሴሆን በፈንድ አስተዳደር እና በሴቶችና በህጻናት ጥቃት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል